Saturday, June 2, 2012

ፊዮሪና

“… ጋራው ቢከልለን ያ ተራራ 
አትወጪም ከሐሳቤ ጓል አስመራ”
ቴዲ አፍሮ-ፊዮሪና
ለዚህ መጣጥፍ መነሻ የሆነኝ ከዛሬ ሰባ ዓመት ገደማ በፊት በ1937 ዓ.ም. ክቡር አቶ ከበደ ሚካኤል (የክብር ዶክተር)  ‹‹የሐማሴን ድምፅ›› በኋላም ‹‹የኤርትራ ድምፅ›› በተባለው ጋዜጣ ላይ ያወጧት ግጥም ናት፡፡ ይህች ጋዜጣ ለኢትዮጵያና ለኤርትራ አንድነት የሚታገሉ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ድምፃቸውን የሚያሰሙባት መድረክ ነበረች፡፡ በአጋጣሚ ለታሪክ ምርምርና ጥናት ሥራዬ በእጄ የገባችው ይህች ጋዜጣ ስለ ትናንትናዎቹ ሁለቱ አገሮች ወደኋሊት በታሪክ ሰረገላ ተጉዤ በጥልቅ እንዳስብ አስገደደኝ፡፡ ይህን በኅሊናዬ እያወጣሁ እያወረድኩ ሳለሁም በቴዲ አፍሮ የተዜሙት ሁለቱ ዜማዎች “ዳህላክ” እና “ፊዮሪና” በአእምሮዬ መመላለስ ያዙ፤ እናም በዚሁ መንፈስ የከበደ ሚካኤል ግጥም፣ የቴዲ አፍሮ ፊዮሪና ዜማና የትናንት ታሪካችን እውነት በውስጤ ያጫረው ስሜት ይህን አጭር መጣጥፍ ሊወልድ ቻለ፡፡ በቅድሚያ ግን በከፊል በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ያካተትሁትን የከበደ ሚካኤልን ግጥም እነሆ ልበል፡-

“እንደነ ኡጋዴን ደግሞ እንደነ ባሌ
ሐማሴን ደሜ ነች ሥጋዬን አካሌ
ይህን ጉልህ ነገር ማነው የሚል አሌ፡፡
…የእሷና የእኔ ቤት ምሰሶው አንድ ነው
አትተዋወቁም የሚለው ሰው ማነው፡፡
…ዘላለም ምን ጊዜም ከዱሮ ከጥንት
በሁለተናችን የለም ልዩነት፡፡
…አንድ አካል መሆኑን የእኔም የእስዋም ገላ
ዶጋሊ ላይ መልካም መስክሯል አሉላ፡፡
…መች ነው የምንገናኝ ከምወዳት እህቴ
አልቆልኝ የማየው የአምሳ ዓመት ናፍቆቴ፡፡”        
ባለቅኔው ከበደ ሚካኤል በዘመናቸው መቼ ነው ምንተያየው ‹‹ከምወዳት እህቴ›› ብለው በናፍቆት ቃል የጠሯትን ሐማሴንን/ኤርትራን ከብዙ ዓመታት በኋላም በታሪክ አጋጣሚ በወጣቱ ከያኒ በቴዲ አፍሮ ዜማ ዳግመኛ በናፍቆትና በስስት እየተነሳች፣ እየተጣለች ነው፡፡ በከበደ ሚካኤልና በቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) መካከል ያለውን የዘመን ልዩነትና በሁለቱ አገሮች የተከሰቱት በርካታ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ለውጦች እንዳሉ ሆነው ግን ሁለቱ አባትና ልጅ በግጥማቸው ያነሷቸው አሳቦች ቢዛመዱብኝና ስሜታቸውን ብጋራቸው ይህችን የታሪክ ሕያው ምስክር የሆነችው በከበደ ሚካኤልን የተጻፈውን ግጥም ለጽሑፌ መነሻ በማድረግ በቴዲ አፍሮ ‹‹ፊዮሪና›› ዜማ ውስጥ ታሪካችን ምን እውነት ይነገረናል በማለት አጭር ቅኝት ለማድረግ ወደድሁ፡፡

ጥበብን አፍቃሪው ቴዎድሮስ ካሳሁን ከሰባት ዓመታት በፊት ‹‹ያስተሰርያል›› በሚለው አልበሙ የአገራችን የዘመናት የመውደቅና የመነሳት ታሪክ፣ ወቅታዊ የሆኑ ፖለቲካዊ ትኩሳቶችንና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን፣ የማኅበረሰባችን የሺሕ ዘመናት እሴቶችና የሕይወት ዋጋዎች ላይ በሙዚቃው ባነሳሳቸው ትላልቅ ቁም ነገሮች የተነሳ የብዙዎችን ቀልብ የገዛና ኪነ ጥበብ የሕዝብ ብሶትና የልብ ትርታ አንደበት የመሆን ሚናዋንና አንድምታዋን ገና በአፍላ ዕድሜው ያለ ፍርሃትና ሥጋት ጥበብ የጣለችበትን አደራ ለመፈጸም የሚታትር የፍቅርና የጥበብ ምርኮኛ መስፍን መሆኑን በሥራዎቹ እያሳየን ያለ ይመስለኛል፡፡

በአገራችን ኢትዮጵያ፣ በመሪዎቻችን፣ በፓርቲዎችና በፖለቲከኞቻችን፣ በሃይማኖት አባቶችና ተቋማት እንዲሁም በእኛና በሕዝባችን መካከል ሊሰፍን ስለሚገባው ፍቅር፣ ሰላም፣ አንድነትና የይቅርታ መንፈስ በሙዚቃዎቹ ድምጹን ከፍ አድርጎ ያሰማው ቴዲ አፍሮ፣ ይቅርታንና ፍቅርን ከመስበክ ባሻገርም በደም፣ በሃይማኖት፣ በባህልና በቋንቋ ስለተሳሰሩት ዛሬም ድረስ በተለይ በቀደሙት ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ዘንድ የማይደበዝዝ ትዝታ የታተሙትን የሁለቱን ሕዝቦች የናፍቆት ስስት እነሱን ሆኖ ይሄን ናፍቆታቸውንና ብሶታቸውን ለመግለጽ የዘመኑ የፖለቲካ ፍርሃት ቆፈን ደማቸውንና ወኔያቸውን ላቀዘቀዘው ወገኖቻችን ድምጽ በመሆን ቴዲ አፍሮ ‹‹ዳህላክና ፊዮሪና›› በሚል ዜማው ለሁለቱ አገሮች ሰላምንና አንድነትን አጥብቆ ሲለምንና ሲመኝ እንሰማዋለን፡፡

ዛሬም ዳግመኛ ‹‹በጥቁር ሰው›› አልበሙ ቴዲ በናፍቆት ስለሚቃጠልላትና በደሙ ውስጥ የሰረጸች ስለምትመስለው ኤርትራ ‹‹ፊዮሪና›› በሚለው ዜማው አስመራን ያንቆለጳጵሳታል፣ በሰቀቀን ያስባታል፣ በናፍቆት ቃልም ይጠራታል፡፡ ያስገረመኝ እኔ እስከማውቀው ቴዲ አፍሮ ኤርትራን በመንፈስ ካልሆነ በአካል ሄዶ እንዳላያትና እንዳልኖረባት እርግጠኛ ነኝ፡፡ ግን እንዲህ አንጀቱ እስኪንሰፈስፍና በትዝታና በናፍቆት ራብ እንዲህ እንደ ሽንብራ እየተንገረገበ ስለ ውቧ አስመራ ማዜሙ ለአንዳንዶች እንቆቅልሽና ጥያቄን የሚያጭር ሆኗል፡፡ እንደውም አንድ ወዳጄ ምናልባት ቴዲ በልጅነቱ ወይ በሰፈራቸው አሊያም በትምህርት ቤቱ በጣም የሚወዳት ኤርትራዊት አሁን ግን በሁለቱ ሀገሮች በተፈጠረው መለያየት የተነሳ ተለይታው የሄደች አንዲት ውብ አስመራዊት ቆንጆ ‹‹ፊያሜታ›› ሳትኖር አትቀርም በቴዲ ልብ ውስጥ እንዲህ ተሰንቅራ እረፍት የነሳችው በማለት ፈገግ አሰኝቶኛል፡፡

በእኔ እሳቤ በእርግጥ እንዲህ ውስጥን በሚንጥ ትዝታና ናፍቆት ውብ አስመራን/ኤርትራን ለማሰብ የግድ እንደ በዓሉ ግርማ በኤርትራ የተፈጥሮ ውበትና የተራሮቿ ግርማና ሞገስ መመሰጥ፣ በሐማሴን፣ በሰራኤና በመንደፈራ እናቶች ፈገግታ፣ እንግዳ ተቀባይነትና ጨዋነት ልብ እንዲጠፋ፣ በአስመራ ከተማ ውበት መዋኘትና በዘንባባዎቿ መካከል መንሸርሸር፣ አሊያም በዳህላክ ደሴቶችና በምጽዋ ባሕር ዳር በነፋሻማ አየር በአሸዋው ላይ መራመድና በደስታ መቦረቅ፣ መፈንጠዝ አለበት/አለብን ብዬ አላስብም፤ ቴዲ አፍሮም ሆነ እኛ፡፡ ትዝ የሚለኝ ከዚህ ጋር በሚመሳሰል ሁናቴ ቴዲ አፍሮ ‹‹ያስተርያል!›› አልበሙን ባወጣ ሰሞን ከሸገር ራዲዮ የጨዋታ ፕሮግራም ላይ ባደረገው ቃለ መጠይቅ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ አንድ ጥያቄ አንስታለት ነበር፤ እንዲህ በማለት፡- ‹‹ቴዲ አንተ ገና ወጣት ነህ በዘፈንህ ውስጥ ደግሞ ስለ ኃይለ ሥላሴ ልክ በዘመናቸው የነበርክና ለዛና ጣእማቸውን የምታውቅ ያህል በስሜት ውስጥ ሆነህ ዘፍነህላቸዋል፤ ይሄ እንዴት ሊሆን ቻለ…›› ቴዲም ሲመልስ፡-
‹‹… በእርግጥ ትክክል ነሽ እንኳን ኃይለ ሥላሴን ለዛና ጣዕም ለማወቅ ቀርቶ በእርሳቸው ዘመን እንኳን ገና አልተወለድኩም፣ አልታሰብኩም ነበር፡፡ ግን ለምሳሌ እኔም አንቺም ክርስቲያኖች ነን፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ደሙን አፍስሶ ቤዛ ስለሆነን ክርስቲያኖች/የእግዚአብሔር ልጆች ለመባል በቅተናል፤ ግና ጌታችን ኢየሱስ ስለ እኛ የከፈለውን ታላቅ የፍቅር ውለታ ለማሰብም ሆነ ክርስቲያን ተብሎ ለመጠራት የግድ የዛሬ ሁለት ሺሕ ዓመት መወለድ ያለብን አይመስለኝም፤ እናም ኃይለ ሥላሴን ለማወደስና ለመዘከር ለእኔ ሥራቸው ከበቂ በላይ ምስክር ይመስለኛል በማለት በጥበብ የተሞላ ምላሽን ለተወዳጇ ጋዜጠኛ ለመዓዛ ሰጥቷት እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡

ስለሆነም ቴዲ አፍሮ ስለ አስመራ ለመዝፈን የግድ አስመራን በአካል ሊያውቃት ይገባል የሚል ጭፍን ተከራካሪ ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡ በቴዲ በልቡ፣ በነፍሱና በደሙ ውስጥ ዘልቃ የገባቸው አስመራ እንዲሁ በድንገት ደርሳ በቴዲም ሆነ በሌሎቻችን ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ አልሰረጸችም፡፡

በበኩሌ ለረጅም ዘመናት በመከላከያ ሚኒስቴር በመኮንንነት በኤርትራ የተለያዩ ግዛቶችና በአስመራ በውትድርና መስክ ለብዙ ዓመታት የቆየው አባቴ ሁሌም ስለ አስመራ ቢናገር የማይሰለቸው እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ የሕዝቡ ሃይማኖተኝነት፣ እንግዳ ተቀባይነት፣ ውብ የሆኑት የአስመራ ከተማ ዘንባባዎች፣ ለጤና ተስማሚ የሆነ አየሯ፣ ማታ ማታ በነፋሻዋማ የአስመራ መንገዶች፣ መዝናኛዎችና በምጽዋ የባሕር ዳርቻ የሚጠጡት የአስመራ መሎቲ ቢራ፣ የምጽዋና የዳህላክ ደሴት የባሕር ዳርቻ የአሸዋው ላይ የተፈጥሮ መኝታና የቀይ ባሕር ላይ የሚታየው የጀንበር መጥለቅ ልዩና መሳጭ የተፈጥሮ ትእይንት ለአባቴ ከልቡ የማይጠፉ ትዝታዎቹና ሁሌም በልዩ አድናቆት ተሞልቶ የሚያወራልን ትዝታው እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡

የቴዲንም ያህል ባይሆን በአባቴ ልብ ውስጥ በትዝታ ነግሣ ሁሌም በአፉ የማትጠፋው ጓል አስመራ በእኔ የልጅነት ልብ ውስጥም ሚጢጢዬ የጉጉትና የናፍቆት ኮረብታን ለመሥራት ችላ እንደነበር ትዝ ይለኛል፣ ከዛም ደግሞ ልጅነቴ አልፎ በሥራና በትምህርት አጋጣሚ በኢትዮጵያ ታሪክና ቅርስ፣ በአፍሪካውያንና በአፍሪካ አሜሪካውያን የነጻነት የፖለቲካ ትግል የማደርጋቸው ጥናቶችና ምርምሮች የአገራችን የረዥም ዘመን ሥልጣኔ፣ አኩሪ የነፃነት ተጋድሎ ታሪክና የዓድዋ ድል በአፍሪካና በጥቁሩ ዓለም ያላቸውን ታላቅ ክብር የሚዘክሩ ያጋጠሙኝና የመረመርኳቸው ታሪካዊ ሰነዶችና መዛግብቶች ደግሞ ይበልጡን ስለ ትናንት እኛነታችን እና ማንነታችን ለመፈተሽ በውስጤ ልዩ ስሜትን አጫሩብኝ፡፡ ‹‹የአደይ ኢትዮጵያ… ጓል አስመራ…!›› መጣጥፍ ውልደትም ውሉ የተመዘዘው በሥራዬ አጋጣሚ ከተፈጠረብኝ ከዚሁ የታሪክ እውቀት ፍቅርና ምርምር የተነሳ ይመስለኛል፡፡

ስለሆነም በሁለቱ ሕዝቦች መካከል የነበረውና አሁንም ያለው ጥብቅ የሆነ ታሪካዊ ትስስር እንደ ድልድይ የቆሙት በደማቸውና በአጥንታቸው ለአገራቸው አንድነት መስዋዕት የሆኑት የእነ አውአሎም፣ የእነ ዘርዓይ ደረስ ፣ የእነ ሞገስ አስገዶምና አብርሃ ደቦጭ፣ የእነ ብላታ ሎሬንሶ ታእዛዝ፣ የእነ ብላታ ኤፍሬም ተወልደ መድኅን፣ የእነ ፊታውራሪ ገ/መስቀል ወልዱ፣ የእነ ዶ/ር ተስፋዬ ገ/እግዚእ፣ ጥቁር አንበሳ መስራቾች መካከል በኋላም በጣሊያን ፋሽስት ከአይሮፕላን ላይ ተወርውሮ እንዲሞት የተደረገው የሌ/ኮሎኔል በላይ ኃይለ አብ …ወዘተ ለቁጥር የሚበዙ በርካታ የሁለቱ አገሮች ጀግኖች በኢትዮጵያና በኤርትራ ምድር በደማቸው የፃፉት ታሪክና የለኮሱት የነፃነትና የአንድነት ቀንዲል በብዙዎቻችን ልብ ውስጥ በታሪክ ቅብብሎሽ ቦግ እልም ስለሚልና በልባችን ጽላት በደም ስለተጻፈ እንጂ፤ መቼም እንዲሁ በድንገት ደርሰን አይመስለኝም ስለ ኤርትራ ሲወራ ደማችን የሚሞቀው፣ መንፈሳችን የሚሸፍተው፡፡

እናም ቴዲ ይህ የታሪክ እውነት በልቡ ተሰንቅሮ እረፍት አልሰጠው ብሎ ይመስለኛል ከአድማስ ማዶ ያለችውን  ኤርትራን ዘንድሮም ‹‹በጥቁር ሰው” አልበሙ፣ በ”ፊዮሪና” ዜማው አስመራን እንዲህ የተቀኘላት፡-
“ከዓይኔ ያራቀሽ መንገድ ያ ጎዳና
ወስዶ ቢነጥልሽ ጓል አስመራ
ጋራው ቢከልለን ያ ተራራ
አትወጪም ከሐሳቤ ጓል አስመራ፡፡”
ቴዲ እነዚህ ሁለቱ የተለያዩ ልቦች የተራራቁ በናፍቆት ትዝታ እየተንገበገቡ ያሉ ነፍሶች አንድ ቀን እንደሚገናኙና ያን ቀንም በተስፋ፣ በስስትና በናፍቆት እንደሚያስበው ይነግረናል እንዲህ ሲል፡-

“ዘመን አልፎ ዘመን እስኪታደስ
ቀኑ ቢመስልም የማይደረስ
በፍቅር ሲቃና መሰረቱ
ደሞ እንደ አዲስ አንድ ይሆናል ቤቱ፡፡”
ምን ዓይነት እምነት፣ ምን ዓይነት ጽኑ ተስፋ፣ እንዴት ያለ ተማጽኖ ነው ቴዲ አፍሮ እየተማጸነ ያለው? በዚህ ሁሉ ተማሕጽኖውና ጭንቅት ውስጥ ደግሞ ቴዲ የዘመን ፖለቲካ፣ የዘመን ውጥንቅጥ ከልቡና ከአካሉ የለያትን ፍቅሩን ጓል አስመራን አንድ ቀን እንደሚያያት በጽኑ ድፍረትና እምነት ሲናገር ይህ ሰው ምን ታይቶት ነው አያሰኝም ትላላችሁ… አሊያም ይህ ልጅ ነቢይ ወይንስ ወልይ ሊሆን ይቃጠዋል እንዴ በማለት ራሳችሁን አልጠየቃችሁም ክቡራን አንባቢዎቼ፡፡

በጽሑፌ ማጠቃለያ ላይ ጥቂት ነገሮችን ለማለት እወዳለሁ፤ ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ የተነሳሁበት ዋንኛው ምክንያት በእነዚህ ሁለት አገሮች ሕዝቦች መካከል ያለው ከብረት የጠነከረና የጋራ የሆነ ታሪካዊ ትስስር፣ ቋንቋ፣ ባህልና ሃይማኖት መሠረት በማድረግ ለጋራ ሰላም፣ እድገትና ብልጽግና የአብሮነትና የወንድማማችነት መንፈስና ትብብር እንዲሰፍን የበኩሌን የብዕር መዋጮ ለማድረግ ከሚል ቅን መንፈስ በመነሳሳት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ የብዙዎቻችን ምኞትና ጸሎት እንደሆነ አስባለሁ፡፡

እንደማስታውሰው በአሜሪካና በአካባቢው በሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ትብብር ግንቦት 7 ቀን 2001 ዓ.ም እና ከመጋቢት 3-5 2002 ዓ.ም. በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት በሳን ሆዜ ‹‹የኢትዮጵያና የኤርትራ የወዳጅነት ጉባኤ›› በሚል የሁለቱ አገሮች ምሁራን ሰፋ ያሉ ጥናታዊ ጽሑፎች ያቀረቡበትና በቀረቡትም ጥናታዊ ጽሑፎች ላይ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ተወላጆች በንቃት የተሳተፉበት ጉባኤ ተካሂዶ እንደነበር ከመረጃ መረብ ላይ ማንበቤብ አስታውሳለሁ፣ በጊዜውም ደስታ ተሰምቶኝ ነበር፡፡

በእነዚህ ሁለት ስብሰባዎች ላይ የጥናት ወረቀታችን ካቀረቡት መካከል ኤርትራዊው ፕ/ር ተስፋ ጽዮን መድኃኔና ኢትዮጵያዊው ምሁር ፕ/ር ዳንኤል ክንዴ ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይም ፕ/ር ዳንኤል ክንዴ በሁለቱ ጉባኤዎች ባቀረቧቸው ጽሑፎች ‹‹የኢትዮጵያና የኤርትራ ፌዴሬሽን አስፈላጊነት›› እና ‹‹ኢትዮጵያና ኤርትራ ከየት ወደየት›› በሚል ርእሶች ያቀረቧቸው ጽሑፎች ለሁለቱ አገሮችም ሆነ ለአፍሪካ ቀንድ አገሮች የወደፊት መፃኢ እድል፣ ሰላምና እድገት ተስፋ ፈንጣቂ የሆኑ እሳቤዎች የተንጸባረቁበት ጥናታዊ ጽሑፎች እንደነበሩ አሁን ከዓመታት በኋላ የጥናት ወረቀቶቻቸውን ሳገላብጥ መገንዘብ ችያለሁ፡፡

ይህ የወዳጅነት ጉባኤ እስከአሁንም ቀጥሎ ይሁን ይቋረጥ መረጃው የለኝም፤ ግና በሀገር ቤትም ሆነ በውጭ አገሮች እንዲህ ዓይነቶች ጉባኤያትና ውይይቶች መልካም ግንኙነቶችንና ሰላምን የሚያሰፍኑ ጉባኤዎችና የስብሰባ መድረኮች መልካም እንደሆኑ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በእጅጉን ያምናል፡፡ በተጨማሪም የሁለቱም አገሮች የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን የጀመሩትን ጥረት አብልጠው ይገፉበት ዘንድ በግሌ አደራ ለማለት እወዳለሁ፡፡ በተጨማሪም እኔና ትውልዴ የትናንትናውን የአገሮቹን ታሪክ ወደኋላ በመጓዝ በማጥናትና በመመርመር መቀራረብና በወንድማማችነት መንፈስ ማውራት የምንችልበት ዕድል ይፈጠር ዘንድ የበኩላችን ጥረት ማድረግ ይገባናል፡፡

ዓለም ስለ አንድነት በሚያወራበት በግሎባላይዜሽን ዘመን እንደገና ልዩነቶቻችንን ማስፋት ጠቃሚ መስሎ አይታየኝም፡፡ ለትምህርት በደቡብ አፍሪካ ቆይታዬ ያየሁትና የታዘብኩት የደስታ ስሜትን ያጫረብኝ አንድ ገጠመኝ አለ፤ ይኸውም በደቡብ አፍሪካ በሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በአንድነት ሆነው አምልኮተ እግዚአብሔር የሚፈጽሙበት የአንድነትና የወንድማማችነት መንፈስ ነው፡፡ እንዲሁም ፕሪቶሪያ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ኤርትራውያን ወጣቶች፣ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችና ሠራተኞች በየሳምንቱ እየተሰባሰቡ በቋንቋቸው እርስ በርሳቸው ሲማማሩና በቤተ ክርስቲያናቱ ዓመታዊ በዓሎችና መንፈሳዊ ጉባኤዎችም ላይ በትግሪኛ ቋንቋ መዝሙር ሲያቀርቡ በማየቴ በጊዜው ልዩ ስሜትን አጭሮብኛል፡፡

እንዲህ ዓይነቶቹን ፍቅርና አንድነት የሞላባቸውን ግንኙነቶች በማጠናከር በኩል የሃይማኖት አባቶች በሕዝብ ዘንድ ያላቸውን ትልቅ ተቀባይነትና ተሰሚነት በመጠቀም በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ያለው ሰላምና ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው ይቀጥሉበት ዘንድ የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ያግዛቸው ለማለት እወዳለሁ፡፡ በማይበጠስ ታሪክ፣ ባህል፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋና ደም የተሳሰርን እኛ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ሕዝቦች ለፍቅር፣ ለሰላምና ለእድገት እጅ ለእጅ የምንያያዝበት ጊዜው አሁን ይመስለኛል፡፡ የእኔን አበቃሁ እስቲ ሌሎችም በዚህ ጉዳይ ላይ ጻፉና በጨዋነትና በቅንነት መንፈስ እንወያይ ለማለት እወዳለሁ…!!!

በዓሉ ግርማ

  Bealu Girma


                        በዓሉ ግርማ                                  (1928 - 1976/)

                 ደራሲ በዓሉ ግርማ በኢላባቡር ክፍለ ሀገር ሱዼ በሚባል ሥፍራ 1928/ ተወለዱ::
ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርሥ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በልዕልት ዘነበወርቅ /ቤት: ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በጄኔራል ዊንጌት /ቤት አጠናቀዋል:: ከዚያም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፖሊቲካል ሳይንስ እና ኢንተርናሽናል ሪሌሽንስ የቢ.. ዲግሪ ያገኙ ሲሆን: በዚሁ ተመሳሳይ መስክ ከአውሮፓ የማስተርስ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል::
ከጻፏቸው በርካታ ድርሰቶቻቸ ውስጥ "ከአድማስ ባሻገር" የተሰኘው መጽሐፋቸው በሩሲያ ዊያ ተተርጉሞ በቀድሞዋ የሶቪየት ሶሺያሊስት ሕብረት ሪፑብሊክ ቀርቧል::
በጋዜጠኝነት
የዛሬይቱ ኢትዮጵያ የመነን መጽሔት የአዲስ ሪፖርተር መጽሔትና;የአዲስ ዘመን ጋዜጣ  ዋና  አዘጋጅና: በኢትዮጵያ ራዲዮም አገልግለዋል::
የመጨረሻው መጽሐፋቸው "ኦሮማይ" በወቅቱ በነበረው የደርግ መንግስት ሊደገፍ ባለመቻሉ: 1976/ ለደራሲው ሕይወት መጥፋት መንስኤ ሊሆን በቅቷል::

ድርሰቶቹ
*
ከአድማስ ባሻገር
*
የኅሊና ደወል
*
የቀይ ኮከብ ጥሪ
*
ሐዲስ
*
ደራሲው
*
ኦሮማይ
        የዚህን ድንቅ ጸሀፊ ልብ ወለዶች ከሞላ ጎደል አንብቤያቸዋለሁ ደራሲ በአሉ ግርማ ልብ የሚመስጥ ልብ ወለድ ጽፎልናል፡፡ እኔ ብዙ ማለት አልችልም የተባለ ለመድገም ካልሆነ ! እጅግ በጣም የሚገርመኝ ግን ገጸ-ባህሪ አሳሳሉ ነው በተለይ ሴት ገጸ ባህሪን ሲስል ያቺ ሴት በእውኑ አለም ያለች ያህል እንዲሰማን የማድረግ ሃይል አለው ምሳሌ ብጠቅስ…………. የአድማስ ባሻገሯ ሉሊት ፤ኦሮማይ ላይ ያለቺውና የነገሰችው መቼም የማትረሳው ፊያሜታን ማንሳት እንችላለን በተለይ ፊያሜታ ጊላይ ምንጊዜም ከህሊናዩ የምትጠፋ አይደለቺም ! በተለይ በአሉ ግርማ በሷ ውስጥ የተናገረባት ፤ የልቡን የውስጡን የተነፈሰባት ደብዳቤዋን እጄ እስኪደማ በወረቀት ገልብጨዋለሁ…….. በተወሰነ ጊዜዎች እስከ ዛሬ ድረስ እያነሳሁ  አነበዋለሁ አይሰለቸኝም !  ምን ይሄ ብቻ ፊያሜታ ጊላይ የምተቀባው ቫኔል ፋይፍ ሽቶ ምን ጊዜም ከህሊና አይረሳም ! ያን ሽቶ አይቼው አሽትቼው ባለውቅም ጥሩ ሽቶ ባየሁ ባሸተትኩ ቁጥር ተመስጫለሁ፤አስቤዋለሁ፡፡ መጽሀፉ በወጣ ሰሞን የሃገሬ ቆነጃጅት ወጣት ሴት ሁሉ በተለይ በመዲናችን አዲስ አበባ ፊያሜታ ምትጠጣውን መሎቲ ቢራ በስፕራይት መጠጣት ፋሺን ሆኖ ፤ሀገሩን አጥለቅልቆት እንደነበር በወቅቱ የነበሩ ሰዎች አጫውተውኛል ፡፡ የዚህን ያህል ደራሲው ገጸ-ባህሪ መሳል ይችልበታል ! ሌሎች ብዙ ልትሉ ትችላላሁ ወይ ብትሉን ደስታዩ ወደር የለውም፡፡ እኔ ግን ፊያሜታን በደራሲው ልብ ውስጥ ሆኘ እያሰብኩ የገጠምኳትን ግጥም በቀጣይ ጊዜ እለጥፈዋለሁ፤ አስነብባችኋለሁ እስከዛው በደራሲው የመጨረሻ ቃል እንሰናበት፡፡
#............;
እንባ እንባ ይለኛል
ይተናነቀኛል………
እንባ ግን የታባቱ
ደርቋል ከረጢቱ
ሳቅ ሳቅም ይለኛል
ስቆ ላይስቅ ጥርሴ
ስቃ እየነደደች
መከረኛ ነፍሴ፡፡
  © © ©
  ኦሮማይ

ስነ-ግጥም…የውበት ልቀት ነው

   ቦንቡን 
ቦንቡን  ካልፈራኸው  ንቀል  ከእንብርቷ
ይቆም  ከመሰለህ  ውበት  መለከቷ
በሸንቃጣ  ወገብ  እንዲህ  ተሞናድላ
በእንጆሪ  ከንፈር  በረዶውን  ስላ
ደረቷ  ሚሳኤል  መያዙን  ሳታውቀው
በአይኗ  ወላፈን  ፍቅርህን  ሳትፈጀው
መሞትን  ከመረጥክ
ትግደልህ  ብያለሁ  እሷም  እንድትገልህ  አንተም  እንደመረጥክ ……


 አቤት ስልጣኔ
የጆሮ ተወዶ  ዘንድሮ  ጉድ ፈላ
ምንስ  የቀረ  አለ  ያልተባሳ  ገላ
ውበት ነው፣እብደት  ነው  ወይስ  ስልጣኔ
ይህው  ጉድ  አሳየኝ ዝቅ  ብሎ  አይኔ
እምብርት  ወግ  ደርሶት  ጉትቻ  አጠለቀ
ተገንጦ  በይፋ  ይህው  ፀሀይ  ሞቀ
ቦዲ  የተባለው  መላ  ቅጡ  የጠፋ
ጡቶቿን  አጋልጦ  ያሳያል  በይፋ
ሚኒ  ደሞ ተብሎ  ጣል  የተደረገው
ሀፍረተ  ስጋዋ ይህው  አጋለጠው።

                                                                             የበረሃዋ ገነት
ከወደ ምስራቅ ጸሀይ መውጫ
ያ'ድማስ ጮራ ህብር መገለጫ
ያላፊ አግዳሚው ፍኖት መሳለጫ
የከረዩ ውበት ያ..ክምክም ጎፈሬ
የኢቱ የአፋር ካፎት የሻጠው ጊሌ
የብሄር ስብጥር የግራር ዛፍ ፍሬ
ከበረሃ መሀል ያለሽው መንደሬ
የ'ትብቴ ማረፍያ እልፍ ዓለም ክትሬ
ከፈንታሌ ጋራ ካዋሽ ወድያ ማዶ
ህብረት እንደ ማገር በፍቅርሽ ተገምዶ
የእህል ውሀ ነገር ካድማስ ወድያ ማዶ
ልቤን ካንቺው ትቼ አካሌ ተሰዶ
ፈገግታ§ን ውÂ ደስታው ከኔ ርቆ
ድንገት ከሳሎኔ ከመስታወት ቆሜ
ጥርሴ ላይ የቀረ ያኖርሺው ማተቤ
ተገልጦ የማያልቅ የህይወት አልበሜ
የማንነት ድርሳን መለያ ቀለሜ
ተዳፍኖ ያለውን የልጅነት ህልሜን
ከፍቼው ልተርክ የትዝታን ኪዳን
ጨልፌው ለመጋት ጥሜን ለአመሌ
ብእር ጦሬን ሰበኩ ዝምታን ሰብሬ፡፡
                                           ከስንኝ ቋጥሬ ቃላት ብዘራልሽ
አደባባይ መሐል ማ‘ሌት ብቆምልሽ
አልሆንልህ አለኝ ጣፋጭ እንደምርትሽ፡፡
መርቲ መተሐራ
አንቺ ገነት የበረሀ
የመቻቻል ባህል የመኖር ስንክሳር
  የሰርቶ ማደግን ካሰቡት የማደር
የእንግዳ አቀባበል መልካም ስነምግባር
እንደ ፈንታሌ ጋራ ዙርያሽ ገዝፎ
ያለ ከልካይ ባዋጅ አየር ላይ ተንሳፎ
 አዋሽ ሆደ ቡቡ አዋሽ ዝምተኛ
አዋሽ ሁላ ሁሉ አዋሽ ሚስጥረኛ
አዋሽ አይታክቴ ምድርሽን ሰንጥቆ
የተጠማን ገላ አንጀት ሆድ አርሶ
አፈርሽን ረስርሶ
በእድገት ላይ ጸጋ ውበትሽን ጨምሮ
ወዛደርሽ ወዙን ሳይቆጥብ ገብሮ
ነገውን በተስፋ በሙዳዩ ቋጥሮ
ፍቅር ሲያስተሳስር ሰግሮ
ዘመን ዘመን ተካ ባ'ንድነት ጠንክሮ፡፡
መርቲ መተሐራ
አንቺ ገነት የበረሀ
የአድባር ከራማሽ ቆሌ
ከጂንፉ ጋራ እስከ ፈንታሌ
ከአባድር እስከ ጮሬ
የለምለም ቄጤማው የአዕዋፋት ዝማሬ
ከበሰቃው ማዶ
ውበትሽ አፍ ገዝቶ
ሲናገር ሰማሁት
ፍቅር ጉልበት ሆኖት፡፡
መርቲ መተሐራ
አንቺ ገነት የበረሀ
ከሙቀትሽ ሞቀን
በንፍጦ ግንፍሌ
ከወንዝሽ ቦጭርቀን
ከመስክሽ ፈንጥዘን
ከስኳርሽ ልሰን
ሸንኮራሽን ግጠን
ስንፈልግ ተጣልተን
ያለ ሽማግሌ ከዋርካው ስር ታርቀን
አሳድገሽናል በመቻቻል ሪቫን
በፍቅርሽ  ተቋጥረን፡፡
አላሳፈሩሽም ወንዝሽን ተሻግረው
አንድ ነው ህልማቸው
አንድ ነው ቋንቋቸው
    መሃላ ቃላቸው
ፍቅርን ይሰብካሉ
ተካፍሎ መብላትን
   ላ‘ለም ያሳያሉ፡፡
እንዲህ እንዳሁኑ ዝናሽ በኛው ገኖ
    ፍቅርሽ እንደ በሰቃ ሰፍቶ
        ኑሪልን በእጥፍ ተባዝቶ፡፡  
 
 

                                                 ጥላ….ሁን ለነፍሴ


ዘመን ዘመነና ከግዜ ደጃፍ ላይ
ትዝታን ቀስቅሶ አይኔ እውነቱን ሊያይ
ለእድሜ እድሜ ይስጠው ለዚህ ቀን ካበቃኝ
እፎ…ይ ልበል በቃ ቋጥሬልህ ስንኝ፡፡
ነፍሴ ጮቤ ረገጠች
ሲቃ ተናነቃት ልቤም ተባረከች
ላለፉት ጣፋጭ ግዜያቶች
ለመድረክ ላይ ገድልህ
አንተን ልታስብህ ቃልት አጣችለት
ደፍሬ ልድፈርህ ነፍሴ ደስ ይበላት፡፡
‘ዋይ…ዋይ ሲሉ የርሀብን ጉንፋን ሲስሉ’
አብረህ ብታለቅስ ቢመጣብህ ምስሉ
‘እሩቅ ምስራቅ’ ሄደህ በመንፈስ አፍቅረህ
በየጦር ግንባሩ በወኔ ታጅበህ
‘ገንዘብ አውጡ ስሩ’
‘ቀጠሮም አክብሩ’
ብለህ አስተምረህ
ካዘነው ስታዝን ከሳቀውም ስቀህ
በዜማ ጽላጼ ለኛነት ታድመህ
እልፍ ሳትነጥፍ አግተህ
ጥ…ላሁን አለችህ እናትህ
ሀሴት ስንሞላ ታይቷት ጥላነትህ፡፡
የልጅነት ግዜን ያፍላነት ቡረቃን
የጣፋጭ ትዝታን የማይጠገብን
በተቀደሰው በሞቀው ፍቅራችን
እጃችን ተቋልፎ አንገት ላንገት ታንቀን
እንባ ግድቡን ጥሶ
ጉንጫችን ረስርሶ
“የህይወቴን ህይወት” እኩል ዘመርንበት
ትፍስትን ለግሶ ሊያገባን ከገነት፡፡
አወይ የመሰጠት መታደል ብዛቱ
እንደ ፏፏቴ ሲፈስ ቃላት ካንደበቱ
በርቦ ተቆንጥሮ ላያልቅ ደግነቱ
ግማሽ ዘመን ሙሉ
እመድረክ ላይ ነግሰህ
ደንሰህ አልቅሰህ
እኛን መስለህ እኛን ኖረህ
ውስጣችን አንኳኩተህ
እርግጥ ነው……
ሰው መቼም ሞትን ይሞታል
ያለነው በፊትም
ሞትን ግን ማሸነፍ
በስራ ተግባሩ
አንተ ድል አድርገህ
                 ዘመን ሲሻገሩ
አየሁት በግርምት እስከሙሉ ክብሩ
እድሜ ጠግቦ ዛሬ በዳግም ትንሳኤ
                ሞትና ልደቱ፡፡
አሀዱ እንዳልክባት እንደ“ጥላ ከለላ”
           ሺ ዘመን ትኖራለህ
ቅርጽ ነህ ላገርህ ሙሽራ ሁን ለኛ፡፡
*   *   *
አደም ሁሴን

እሳት ወይ አበባ


እሳት ወይ አበባ

 ሌት ከዋክብቱ  እንደ ፀደይ
አጥለቅልቆን  በቀይ አደይ
ሰማዩ  ሥጋጃ  አጥልቆ
ተሽለምልሞ  አንጸባርቆ
ፈክቶ አሸብርቆ  ደምቆ
በአዝመራ  በአጥቢያ  ዐፀድ  ሰፍኖ
የዓደይ  አዝርዕት  ተከሽኖ
በዕንቁጣጣሽ  ሰብል  ታጥኖ
ኢዮሃ  አበባዬ  ሆኖ፥
ጨረቃዋ  ከቆባዋ፥  ከሽልምልሚት  እምቡጧ
ብላ ከሰንኮፈንዋ፥ ተንዠርግጎ የእንኮይ ቡጧ፥
ድንግል  ጽጌ-ረዳ  ፈልቃ
ፍልቅልቂት  ድምቡል ቦቃ
ተንሠራፍታ  የአበባ  ጮርቃ፥
ታድያን  ብሌኑ  የጠጠረ
ባሕረ-ሃሳቡ የከረረ
የውበት ዓይኑ የታወረ
ልበ-ሕሊናው  የሰለለ
አይ፥ አበባ አይደለም አለ፤
አይ፥ እሳት አይደለም አለ፤
ያልታደለ።
ሰማይ  ጨለማ  ነው እንጂ፥  እሳት አደል ብሎ ካደ
እቶን  ባይኑ  እየነደደ።
ከዋክብቱ  እንደ  ችቦ
በነበልባል  ወርቀ  ዘቦ
ከፅንፍ  ፅንፍ  አውለብልቦ
ደመራው  እየተመመ
እየፋመ  እየጋመ
ደመና  እንደንዳድ  ሲነድ
መንጸባርቅ  ሰደድ  ሲወርድ፥
በራሪ  ኮከብ  ተኩሶ
በአድማሳት  እሳት  ለኩሶ
ይኸ እንደኔና  እንዳንቺው፥  የውበት ዓይኑ  የሰለለ
ሰማይ ጨለማ ነው እንጂ፥  እሳት እኮ አይደለም አለ፥
ያልታደለ።

ይቅር ብቻ  አንናገርም፥
እኔና  አንቺ  አንወያይም፤
ለውይይት  አልታደልንም
እንዲያው ዝም፥ እንዲያው ዝምዝም።
አበባ አንሆን ወይ እሳት
ተጠምደን  በምኞት  ቅጣት
ሰመመን  ባጫረው  መዓት
ዕድሜ አችንን እንዳማጥናት፤

እሳት አንሆን ወይ አበባ
በሕቅ  እንቅ  ስንባባ
ባከነች  ልጅነታችን፥ እየቃተትን ስናነባ
ሳንፈጠር  በሞትንባት
ሳናብብ  በረገፍንባት
ሳንጠና ባረጀንባት
አበባ ወይንም እሳት፥  መሆኑን ብቻ አጣንባት።
© © ©

ከጸጋዬ ገብረ መድኅን