Thursday, August 16, 2012

የፓትርያሪኩ እረፍት


ብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ፓትርያሪክ ርእሰ ሊቀ ጳጳስ ዘኢትዮጵያ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሓይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ፕሬዘዳንት እና የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዘዳንት ንጋት ላይ አርፈዋል፡፡
እግዚአብሔር ነፍሳቸውን ይማር! 
አባ ጳውሎስ ባደረባቸው ህመም ዛሬ ነሐሴ 10 ከንጋቱ 11.00 ሰዓት ላይ በ76 ዓመታቸው አርፈዋል፡፡

ባለፈው እሁደ ነሐሴ 6 2004 የመጨረሻ የቅዳሴ ሰነስርአቱን በቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም የመሩት ብፁዕነታቸው ቤተ ክርስቲያናችንንም በፓትርክና ለ20 አመታት ያህል ሲገለግሉ ነበር፡፡
ጠዋት ላይም እንዳስነበብናችሁ ፓትሪያርኩ ማረፋቸውን ገልጸንላችኋል ከስፍራው ተገኝተን የቅዱስነታቸውን ዕረፍት አስመልክቶ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ዛሬ ረፋዱ ላይ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አዳራሽ ለተገኙት ለአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች እንዲሁም ለምእመናንና ምእመናት ባስተላለፉት መልእክት የቅዱስ ፖትርያርኩ ዕረፍት የመላው ዓለምና የቤተ ክርስቲያኒቱ ኀዘን መሆኑን ገልጸው የቀብራቸውን ቀን እና ስነስረአት አስመልክቶና ተያያዥ ጉዳዮችን በቀጣይ የሚገለጽ እንደሆነ እና አሃት አብያተ ቤተክርሲቲያናት እና የአለም ሃይማኖቶች የሰላም አባቶች ተወካዮቻቸውን እስከሚልኩ የሚጠበቅ መሆኑን ተገልጧል፡፡
በስፍራውም በነበርንበት ሰዓት ከፍተኛ ሀዘን የሚታይ ሲሆን ብዙዎችም በእንባ ታጥበው ጮኽው በማልቀስ ላይ ነበሩ ፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ቅዱስነታቸው ማረፋቸው በአሁኑ ሰዓት ካለው የቤተክርስቲያን ሁኔታ አንፃር ብዙዎች ነገር በስጋት ላይ ይገኛሉ፡፡
ብዙዎቹን እንደሚያሰጋውም የፓትሪያርኩ ደጋፊዎች የነበሩ ክፍተቱን ተጠቅመው ሊፈጥሩት የሚችሉት ብጥብጥና ተጽእኖ በቤተክርስቲያን ላይ ግጭት እንዳይነሳና ምክንያት እንዳይሆን ተፈርቶአል፡፡
ሌሎችም ስልጣናቸውን ተጠቅመው ድብቅ ሴራቸውን እና ቤተክርስቲያንን ወደ ማያባራ ችግር እንዳይከቷት የቤተክርሲቲያን አባቶች ሊያስቡበት እንደሚገባ እየተነገረ ነው፡፡
ይህንኑ ተከትሎ የቤተክርስቲያናችንን ታላላቅ ቅርሶችና ሀብቶች ሊያሸሹ የሚችሉ ኃይሎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ተፈርቶአል፡፡
ምንም እንኳን የቅዱስነታቸው እረፈት ያልታሰበ አደጋ ቢሆንም ከዋልድባ  ገዳም ላይ ሊገነባ ከታሰበው የስኳር ፋብሪካ  ጉዳይ ጋርም ያያዙትም አሉ፡፡
ሌላው ቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ በቤተክርሲቲያኗን ላይ ሊደርሱት የሚችሉት ችግሮች ከመታደግ አንፃር  ውሳኔ እንደሚያስተላልፍ እና ምዕመናኑን ሊያረጋጉ እንደሚችሉ  ይጠበቃል፡፡ 
ከዛሬ ጀምሮ ቅዱስ ሲኖዶስም ወይይት እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡ 
በቀጣይስ ማን በወንበሩ ይቀመጣል?
በ1991 ዓ.ም የወጣውና በሥራ ላይ የሚገኘው ሕገ ቤተ ክርስቲያን
ፓትርያርክ ድኅረ ዕረፍት ወይም ከሥልጣን መውረድ (አንቀጽ 16) ኹኔታዎች
በአንቀጽ 17 ንኡስ አንቀጽ 1 – 3 የሚከተለውን ይላል፡፡
 
አንቀጽ 17 - ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ
  1. ፓትርያርኩ በሞት ሲለይ ወይም በዚህ ሕግ አንቀጽ 16 መሠረት ከሥልጣኑ ሲወርድ ቅዱስ ሲኖዶስ በሹመት ቀደምትነት ካላቸው ሊቃነ ጳጳሳት መካከል በዕለቱ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ መርጦ ይሾማል፡፡ የተተኪው ፓትርያርክ ምርጨም ይካሄዳል፡፡
  2.  ተተኪው ፓትርያርክ ምርጫ አፈጻጸም እንደጊዜውና እንደ ሥራው ኹኔታ እየታየ ከ40 እስከ 80 ቀን ባለው ጊዜ ይኾናል፡                                                                                        የዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩ ተግባር፡-
ሀ) ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ጊዜያዊ ጉዳዮችን ከቋሚ ሲኖዶስ ጋራ እየመከረ ያከናውናል፡፡
ለ) በፓትርያርኩ ምርጫ ጊዜም የቅዱስ ሲኖዶስ ሊቀ መንበር ኾኖ ምርጫውን ያስፈጽማል፤ እርሱ ግን ከምርጫው አይገባም፡፡
ሌሎች ዜናዎችን ይጠብቁን
ቸር ወሬን ያሰማን፡፡

No comments:

Post a Comment