Friday, May 25, 2012

ቴዲ አፍሮ -ስለ ፍቅር

በፍቅር ለይኩን
                                      
fikirbefikir@gmail.com

           
ልክ እንደ አክሱም ራስ ቀርጸሃት ራሴን፣
በፍቅር ጧፍ ለኩሳት ነፍሴን…፡፡


ቴዲ አፍሮ ስለየትኛው ፍቅር ሊነግረን፤ በየትኛውስ የፍቅር ጧፍ/እሳት ነው ሊለኮስ፣ ሊቀጣጠልና ሊነድ የፈለገው?
     ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) በብዙዎች ሙዚቃ አፍቃሪያን ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ወጣት ከያኒ ነው፤ በሙዚቃዎቹ በሚያነሳው ሀገራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ታሪካዊና ወቅታዊ ጉዳዮች የተነሳ የብዙዎችን ቀልብ ለመግዛት የቻለ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ የተነሳም የቴዲ ጥቁር ሰው አልበም በትልቅ ናፍቆትና ዘንድሮስ እንደ ትላትናው አሊያም ከበፊቱ በበለጠ በሙዚቃ ስራዎቹ ምን ይዞልን ይመጣ ይሆን በሚል ጉጉት ነበር የተጠበቀው፡፡ ቴዲ የተጠበቀውን ያህል በሙዚቃው የአድማጮቹን ልብ አርክቷል ወይስይህ የዚህ ጹሑፍ ዓላማ፣ ጥያቄም፣ የማወቅም ፍላጎት አይደለም፡፡
ይልቁንም ለዚህ አጭር መጣጥፍ መነሻ የሆነኝ ቴዲ ስለ ፍቅር በሚለው ዘፈኑ ያነሳሳቸው ጥልቅ የሆኑ፣ ውብና ስሜትን የሚኮረኩሩ ግጥሞቹ ብዕሬን ከወረቀት እንዳገናኝ ስላስገደዱኝ ነው፡፡ ከዛ በፊት ግን ቴዲ አፍሮ በአንድ ወቅት ስለ ሙዚቃና ዘፋኝነት ከክርስትና ሃይማኖት አስተምህሮ  አንፃር በአንድ ወቅት ከአንድ መጽሔት ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ ዘፈን ኃጢአት ነው ይላል መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ጉዳይ ላይ አንተ ምን ትላለህ ተብሎ ለተጠየቀው ጥያቄ ቴዎድሮስ ካሣሁን የሰጠውን ምላሽ በአጭሩ ለመጥቀስ እወዳለሁ፡-
. . . ሙዚቃ የነፍስ ቋንቋ ነው፣ የሙዚቃ መገኛም እግዚአብሔር ነው፡፡ አምላክም ሙዚቃን ለራሱ ለምስጋና የፈጠረው ይመስለኛል፡፡ እግዚአብሔር ከፍጥረት በፊት ጀምሮ ምስጋናው የባሕርይው ነው፣ መላእክትንም የእግዚአብሔር አመስጋኝ ፍጥረቶቹ ናቸው፡፡ ፍጥረት ሁሉ የየራሱ ዜማ አለው፣ አእዋፍት፣ እጽዋዕት፣ ውቅያኖሶች፣ ባሕሮች፣ ተራሮችእነዚህ ሁሉ እንዲሁም ከሁሉም በላይ ደግሞ የፍጥረት ቁንጮ የሆነው ሰው እግዚአብሔርን እና ውብ፣ ድንቅና ፍቅር የሞላበትን የእጆቹን ሥራዎች  ለማመስገን የተሰጣቸው ቋንቋ ሙዚቃ ነው፡፡ እኔም በሙዚቃዬ የመጨረሻ ዓላማዬና ግቤ ይሄን እግዚአብሔርን መፈለግና ማግኘት ነው፡፡ በማለት ማብራራቱ ትዝ ይለኛል፡፡
ቴዲ በሙዚቃው እፈልገዋለሁ፣ አገኘዋለሁ ያለውን ፈጣሪን አግኝቶት ይሆን ወይስየቴዲ የግል ምስጢሩ እንደሆነ አስባለሁ
ግና በሙዚቃው የአምላክ የመጨረሻ ፍቅርና ጥበብ ስለፈሰሰበትና ስለተገለጸበት ስለ ሰው ልጅ አስደናቂ የፍቅር ውበትና ነጸብራቅ፣ በፍቅር ልዩ ድርስት ስለተዋቡት ስለ ተፈጥሮ ድንቅ ውበትና የአምላክ የእጆቹ ስራዎች አድናቆቱ፣ መመሰጡ፣ ቅኔ መቀኘቱ፣ ዜማ መደርደሩ የሚበቃና የሚያበቃ አይደለም፡፡ ትናት የነበሩ ከያኒያን፣ ጸሐፍት፣ ሰዓሊያን የፍቅርን ውበትና ጥበብ በብእራቸው፣ በብሩሻቸው፣ በዜማቸው፣ በቅኔያቸው ከፍጥረት ማግስት ጀምሮ ተቀኝተዋል፣ ተጠበዋል፣ ተመስጠዋል በአድናቆትም ከራሳቸው ተሰደዋል፣ ጠፍተዋል፡፡ ዛሬም እንዲሁ ቀጥሏል ገና ስለ ፍቅር ለዘላለምም ይጻፋል፣ ቅኔ ይደረደራል፣ ይዜማልፍቅር የዘላለም ውበት የዘላለም ቋንቋ፣ የዘላለም ጥበብ ነውና…!!!  
ቴዲ ስለ ሙዚቃና ስለ ዘፋኝነቱ የሰጠውን ቃለ መጠይቅ ቃል በቃል ሙሉ ለሙሉ ገልጬዋለሁ ለማለት ባልችልም በወቅቱ ካነበብኩትና ከማስታውሰው አንጻር በቃለ መጠይቁ ስለ ሙዚቃና ዘፋኝነቱ የሰጠው ማብራሪያ ይህንኑ የሚመስል ይመስለኛል በእኔ አገላለጽ፣ በእኔ ትውስታ፡፡ ስለ ዘፈን ወይም ዘፋኝነት ከክርስትና ሃይማኖት አስተምህሮ አንጻር ያለውን አንድምታና ትርጓሜ እንዲሁም በሁለት ጫፍ ላይ በቆሙት ክርክሮች ዙሪያ በዚህ በዛሬው ጹሑፌ የምለው ነገር የለኝም፤ ስለሆነም ይኸው ዘፋኝነትና ዘፈን ከክርስትና ሃይማኖት አስተምህሮ አንጻር እንዴት ይዳኛል የሚለውን ጅምር እሳቤዬን በዚሁ ልግታና ለዚህ መጣጥፌ መነሻ ስለሆነኝ ቴዲ አፍሮ በጥቁር ሰው አልበሙ ስለ ፍቅር በሚለው ዘፈኑ ስለ ፍቅር ያነሳሳቸውን ነፍስ ድረስ የሚዘልቁ መልእክቶቹ ዙሪያ ጥቂት ነገሮች ለማለት ፈልገሁ፡፡ እናም ስለ ፍቅር በፍቅር ወደ ቴዲ አፍሮ የፍቅር ግጥሞች ቅኝት አብረን እናዝግም፡፡
ወጣቱና በብዙዎች ዘንድ ተፈቃሪ የሆነው ቴዲ አፍሮ ‹‹ስለ ፍቅር›› በሚለው ዜማው የውስጥ ጩኸቱን፣ የነፍሱን እሪታ፣ የመንፈሱን ጭንቀትና ምጥ ከራሱ አልፎ ለወገኑ፣ ለሀገሩ እንዲያም ሲል ለሰው ልጆች ሁሉ ይሰማለት ዘንድ የፍቅርን ጩኸት ከእያንዳንዳችን የልባችን ጓዳ ይደርስ ዘንድ መልእክቱን ስለ ፍቅር በሚለው ዜማ እነሆኝ ብሏል፡፡ በእለተ ትንሣኤ ከሸገር 102.1 ሬዲዮ ከጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ ጋር ባደረገው አጭር ቃለ ምልልስም ቴዲ ስለ አልበሙ ሲጠየቅ ፍቅርን ነው የሰበከው በሥራውም ፍቅርን ነው እንደ ሰንደቀ ዓላማ ከፍ አድረጎ ሊያሳየን የወደደው፤ እንዲህ ሲል፡- ‹… በዚህ አልበም ውስጥ በብዛት የተካተቱት ሥራዎች ፍቅር ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ከምንም በላይ ፍቅር ያስፈልገናል፤ ሕብረት ያስፈልገናል፡፡ ፍቅር ራሱ ያለ ሕብረት የሚገለጽ ነገር አይደለምና፡፡››
ከያኒው በዚህ ስለ ፍቅር በሚለው ሙዚቃው ሊነገረን የፈለገው/የወደደው ፍቅር ስለ ጊዜያዊው ፍቅር፣ በአፋችን ሞልቶ በልባችን ሥፍራ ስላጣው ወይም ስሜታዊነት ሰለሚጎላበት ግሪካውያኑ ኤሮቲክ ብለው ስለሚጠሩት የፍቅር ዓይነት አይደለም፡፡ ይልቁንም ነፍሱ እንደ ጧፍ ትንድበትና ትቀጣጠልበት ዘንድ ስለሚሻውና ስለሚማጸንላት መለኮታዊ ስለሆነው፡- ታማኝነት፣ ትህትና፣ ይቅር ባይነትን፣ ትዕግስትን፣ ታጋሽነትን ስለተሞላው፣ ሁሉን ተስፋ ስለሚያደረገው፣ በሁሉ ስለሚታመነውና በሁሉ ስለሚጸናው ዘላለማዊ ፍቅር እንጂ፡፡ እናም ይህን ፍቅር ለመተረክ ነፍሱ እንዳትዝል የሚማጸነው ቴዲ ከፍጥረት ማግስት ጀምሮ ፍቅርን ሊተርክልን በብዙ ሺህ ዘመናት ወደኋሊት አንደርድሮ ርዕሰ አበው፣ የእምነት አባት የሚል መጠሪያ ወደተሰጠው ወደ እስራኤላውያኑ አባት ወደ አብርሃም ዘመን በምናብ ወደኋሊት ይዞን ይጓዛል፡፡ የአብርሃምን በመታዘዝ ፍቅር የተዋበውን የእምነት ገድሉንና ከዘመናት በፊት እንደ ሰንደቀ ዓላማ ከፍ ብሎ ደምቆና ተውቦ የታየውን ፍጹም የሆነውን መለኮታዊውን ፍቅር በመመኘት ነፍሱ በዚህ ፍቅር ጧፍ እሳት ትለኮስ፣ ትቀጣጠልና ትነድ ዘንድ ጹኑ ምኞቱን፣ ኤሎሄውን ለነፍሱና ለሚሰማው ሁሉ ይጮኻል እንዲህ ሲል፡-
አንተ አብርሃም የኦሪት ሰባት
የእነ
እስማኤል የይስሐቅ አባት
ልክ
እንደ አክሱም ራስ ቀርጸሃት ራሴን
በፍቅር
ጧፍ ለኩሳት ነፍሴን
በል አትዛል ቀና ሁን ልቤ
የህልሜን
ከነአን እንዳይ ቀርቤ፡፡
ከያኒው አብርሃም በእምነት ዓይን አሻግሮ ያያትንና በሩቅ የተሳለማትን እንዲሁም የቀደሙ እስራኤላውያን በእምነት በሆነ መታዘዝ የወረሱትን ከነዓንን ተርኮልን ብቻ አያቆምም እሱም ለነፍሱ የሚመኝላትን፣ በሩቅ ሆኖ በናፍቆት የሚቃጠልላትን፣ የሌትና የቀን ህልሙ የሆነች ከነዓኑን በፍቅር ይወርሳት ዘንድ ነፍሱ ትበረታ ዘንድ ስለ ፍቅር ደከመኝ፣ አመመኝ፣ ሰለቸኝ ሳትል የሩቅ ህልሟን ከነዓኗን በተስፋዋና በቃል ኪዳኗ ጸንታ ትውርሰው ዘንድ ይማጸናል፡፡ እናም መቼም ቢሆን ስለ ፍቅር የምትዝል ልብ፣ የምትደክም ነፍስ እንዳትኖረው በብርቱ ይጨነቃል፣ ይጮኻል፣ ያምጣል፡፡ ስለ ነፍሱ የፍቅር ርሃብና ጥማት ብርቱ ጩኸትን ጮኾ እኛንም እንድንጮኽ የፍቅርን አዋጅ ዜማ በነፍሳችን ውስጥ ይንቆረቀቆር ዘንድ በፍቅር ስለ ፍቅር ልቡ እየደማች፣ ነፍሱ እያቃሰተች ይቀኛል፣ ያዜማል፡፡
በእጅጉ የደነቀኝ ቴዲ በፍቅር እጦት የተጎሳቆለች ነፍሱን፣ ሀገሩንና ሕዝቡን በታሪክ መነጽር እየቃኘ በጊዜ ሀዲድ ላይ ለሺህ ዓመታት ተጉዞ ከአክሱም የሥልጣኔ ጫፍ ተነስቶ፣ በጎንደር ፋሲለደስ ስልጣኔ፣ ጥበብና ጽኑ የሃይማኖት ገድል ባሕር በመዋኘት የትናቱ የእኛ ጥበብ መሰረቱ የቱ ላይ እንደሆነ እንምመረምር ዘንድ አናግሮ ያናግረናል፣ እርስ በርሳችን ያነጋግረናልም፡፡ ፍቅርን እና እውነትን በየትኛው የታሪካችን ዘመን አሽቀንጥረን እንደጣልነው ተጠየቁ እንጠየቅ ይለናል፡፡ የሺህ ዘመናት ስልጣኔያችንና ታሪካችን፣ ጥበባችን በፍቅር፣ ፍቅራችን በጥበብ የተገመደበት ውሉ ከየት ተጀምሮ የት እንደተቋረጠ ታሪክን እንጠይቅ ዘንድ እንዲህ ሲል በቅኔው ተመራምሮ ያመራምረናል፡-
ብራናው ይነበብ ተዘርግቶ ባትሮኖሱ ላይ፣
የእነ
ፋሲለደስ የእነ ተዋናይ፣
የት
ጋር እንደሆነ ይታይ የእኛ ጥበብ መሰረቱ፡፡
እናም እስቲ ታሪክ ይታይ፣ ይመርመር፣ ዘመናትን ያስረጁና የተሻገሩ ብራናዎቻችን ይውጡ፣ የሺህ ዘመን የሃይማኖት፣ የጥበብ፣ የታሪክ፣ የሥልጣኔና የፍልስፍና ድርሳኖቻንን ይታዩ ይመርመሩበአክሱም ስልጣኔ፣ በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ትንግርት፣ በጎንደር በእነ ፋሲለደስ የስልጣኔ አየር ዝናዋ የናኘላት፣ እነዛ ፍቅርን በጥበብ አስውበው በቅኔያቸውና በማኅሌታቸው ሰማይ ሰማያትን ሰንጥቀው በመንፈሳቸው ጸባዖት የደረሱ በፍቅር ጧፍ የነደዱ በማሕሌታዩ ያሬድ መንፈስ የተነሱ እንደ ተዋናይ ያሉ የቅኔ የጥበብ ጉልላቶች እንደ አጥቢያ ኮከብ በደመቁባት ምድር ዛሬን ፍቅር የተራብን፣ ጥበብን የተራቆትን፣ ስለ ፍቅር የደከመን ምንድነው ምክንያቱ የሚል ይመስለኛል ቴዲ፡፡
ቴዲ በሙዚቃው ለታሪክ ያለውን ስሱነትና (sensitivity) እውቀትም (Indigenous Knowledge) አሳይቶናል፡፡ ተዋናይን ስንቶቻችን እናውቀዋለን ተብለን ብንጠየቅ  የሚያስተዛዝበን ሳይሆን ይቀራል፡፡ በተለይ ደግሞ ለዘመናችን ትውልድ ለአፉም ለልቡም ቅርቦቹ እነ አርሴናል፣ ቼልሲ፣ ሜሲ፣ ሮናልዶ፣ እነ ፊፍቲ ሴንት እነ ቢዮንሴ፣ ወዘተየባሕር ማዶዎቹ ዝነኞች ናቸው እንጂ እነ ተዋናይን እነ ቅዱስ ያሬድን፣ እነ አጼ ፋሲልን ሊያስባቸው ወኔው ያለው አይመስልም፣ ኅሊናውንም ይደክመዋል እናስ እንዴት፣ ምን ሲደረግስ ሊያስባቸው ይችላል የኔ ትውልድ፡፡ በቅኔው የተራቀቀና በመንፈሳዊ እውቀቱ አንቱ ስለተባለው ስለ ተዋናይ ለመስማትም ሆነ ለማወቅ የታሪክ መዛግብትን ማገላበጥ ግድ ይላል፡፡ አሊያም ከቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት አባቶች እግር ስር ቁጭ ማለት ያስፈልግ ይመስለኛል፡፡
ቴዲ በየትኛው መንገድ የሀገሩንና የቤተ ክርስቲያኑን የጥበብ እና የሥልጣኔ ከዋክብቶችን ሊያውቅ እንደቻለ ባይነገረንም የትናንትናዎቹን የሀገራችንን ባለውለታዎችና የዘመን ፈርጦች ማንነት ለማወቅ እና እንዲሁም ታሪኩን ለመመርመር ግን የተጋና የሰላ አእምሮ እንደተቸረው/እንዳለው የግጥሞቹ መልእክቶች ይነግሩናል፡፡ እናም ከታሪካችንና ከስልጣኔያችን መሰረት ከአክሱም ተነስቶ በጊዜና በታሪክ ሃዲድ ላይ አሳፍሮን በትላንት ታሪካችን ውስጥ ራሳችንን እንድንመረምር፤ ራሳችንን እንድናይ ይወተውተናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ይለናል ቴዲ ስለ ፍቅር ዜማው ውብ የግጥሞቹ ስንኞች፡-
. . .የኋለው ከሌለ የለም የፊቱ፣
ሳይራመድ
በታሪክ ምንጣፍ፣
ሰው
አይደርስም ከዛሬ ደጃፍ፡፡
በማለት ከታሪካችን ጋር እጅ ለእጅ በምናብ ሊያጨባብጠንና ሊያስተያየን ይፈልጋል፤ እናም ያለ ትላንት ዛሬ የለም፣ ያለ ዛሬ ደግሞ ነገ አይታሰብም በሚል የመጣንበትና የተጓዝንበትን አኩሪና አሳፋሪ የታሪካችንን ምእራፍ ለማገላበጥ ለደከምን ለእራሱ እና ለእኛ ትልቅ ቁም ነገር ያለው ምክር ያስተላልፋል፡፡ ይህ የከያኒው የግጥም ስንኝ የሮማውን ታላቅ የሕግ ሊቅ፣ ፈላስፋና አስተማሪ የሆነውን የሲስሮን አባባል አስታወሰኝ፡- ከመወለዳችን በፊት ያለውን ታሪክ ካላወቅን ዕድሜ ልካችንን ሕጻን ሆነን እንቀራለን፡፡›› ታሪካችንን ለመመርመር እና ከታሪካችን ለመማር የደከምን እኛ ዛሬም እንደ አዲስ ሰናፈርስ ስንጀምር ከመጀመር ሳንወጣ እንደ ህጻን ባለህበት እረገጥ የሆንበትና ታሪክን እንድንደግም የተፈረደብን ምስጢሩ ምን ይሆን በማለት ታሪክ ጠያቂ፣ የታሪክ ወዳጅ፣ ከታሪክ የምንማር እንድንሆን ያተጋናል፡፡
ከምንኮራበት ታሪካችንና ስልጣኔያችን ባልተናነሰ አንገት የሚያስደፋ ስማችንና ማንንታችን በዓለም ፊት በቀየረብን በበርካታ የራብ፣ የእርስ በርስ ጦርነትና መበላላት ታሪክ ዘመናትን ውስጥ አልፈናል፡፡ እናም የመጣንበት መንገዱ ረጅም ዘመናቶቻችንም መከራ ሰቆቃና ዋይታ የነገሰባቸው ናቸው ሲል   የትናንቱን አሳፋሪ ታሪክ ለመድገም የተፈረደብን ይመስል ታሪክ ደጋሚዎች እንድንሆን የሆንበትን እውነታ መመርመርና ማየት እንችል ዘንድ ትልቅ ጥያቄ ያጭርብናል፡፡  ዛሬም እግራችን መሄድ ተስኖት ቆመናል፤ የመጣነው መንገድ ረጅም አሳዛኝና መራርም ነው፡፡ ለም አፈር ክረምት ከበጋ የሚፈሱ ወንዞች እያሉን ተረበናል ተጠምተናልምክንያቱ ምን ይሆንእስቲ እንጠይቅ፣ እንጠያየቅ እያለ ይመስለኛል ቴዲ
አጥተናል እውነት ነው ተቸግረን ብዙ አይተናል፣
የመጣነው
መንገድ ያሳዝናል፡፡
እግር
ይዞ እንዴት አይሄድም፣
ሰው
ወደፊት አይራመድም፡፡
አፈር
ይዞ ውስጡ አረንጓዴ፣
ለምን
ይሆን የራበው ሆዴ . . .፡፡
ሲል ይጠይቃል ቴዲ፣ ይህ የሁላችንም ጥያቄ ይመስለኛል፡፡ ምዕራባውያን መጽዋቾቻችን ዘንድ The Green Famine አረንጓዴዋ ግን ራህብተኛዋ ሀገር በሚል ቅጽል ለምትታወቀው ሀገራችን ለበርካታ ጊዜያት ዓለም አንብቶላታል፣ የምጽዋት እጆችም ተዘርግቶላታል፡፡ በራብ የተነሳ ከነበርንበት የክብር ሰገነት ተሸንቀጥረን የወደቅን፣ ጣእረ ሞት ያንዣበብን እኛን ያዩ ሁሉ እንባ የተራጩልን፤ ስማችን ዝናችን የተለወጠብን ዓለም በራብና በጦርነትና በመለያየት ጥቁር መዝገቡ ያሰፈረን ሕዝቦች ነን፣ ከዚህ አሳፋሪ ታሪክ ለመውጣትና ስማችንን ለማደስም በፍቅር እጅ ለእጅ ለመያያዝና ይቅር ለመባባል እጅጉን ደክመናል፣ ታክቶናል እናም ይላል በትናንትናው በዛሬውም መልእክቱ ቴዲ፡-
በፍቅር እና በጥበብ በስልጣኔና የታሪክ ከፍታ በአክሱም፣ በላሊበላ በጎንደር ከፍ ብሎ የታየ ሕዝብ ዛሬ አንገቱን የደፋው ፍቅርን ቢያጣ፣ ፍቅርን ቢራብ እንጂ በሌላ አይደለም የሚል ይመስላል ቴዲ፤ ይህ የከያኒው የውስጥ ብሶት በአንድ ወቅት / ፈቃደ አዘዘ ዐሻራ በሚለው የግጥም መድብሉ የተቀኘውን ስንኞች አስታወሰኝ፤ ስለ ፍቅር ስለ ሰላም ስለ እድገታችን ደጋግመን የዘመርን፣ ቃለ መሃላን የገባን ግን የፍቅርን ጎዳናን በእውነትና በሥራ መኖር፣ መግለጽ ለታከተን፣ ለደከምን ለእኛ እንዲህ ተቀኝቶ ነበር፡-
ውበት ልምላሜ
ፍቅር
ብልጽግናን
ሰላምና
እፎይታን
ባፋችን
አሳደን
አሳደን
አሳደን
መያዙ
ቢያቅተን፤
ያው
እንታያለን!!!
አኩፋዳ ይዘን፤
በነውር
ተንቆጥቁጠን
በርዛት አጊጠን
በጦር ተኩነስንሰን
በሬሳ አሸብርቀን
እናም ስለ ፍቅር ባወራን፣ ስለ ፍቅር ጽዋችንን ከፍ አድረገን ባነሳን ማግስት ወደ መለያየት፣ እርስ በርስ ወደመጠፋፋትና ወደ ጠብ የገባንበት ምስጢሩ ምንድነው ስለ ፍቅር ሲወራ ጠብ ጠብ የሚሸተን፣ በአንድነት ስም መለያያየት፣ ጠብና ጥላቻ ከሆነ ማውራት የሚቀናን መንገዱን ስተናል፣ የፍቅራችንን፣ የሰላማችንን፣ የእድገታችንንእናም፡-


ስለ ፍቅር ሲባል ስለ ጸብ ካወራን ተሳስተናል፣
አንድ ላይ ብንሆንም ተለያይተናል፡፡
በማለት ከፍቅር ጋር ማዶ ለማዶ የቆምንበትን ከትናንት ታሪካችንና ከዛሬ ካለንበት ዘመናችን ጋር እያስተያየ ለፍቅር እንበርታ አንድከም ይላልአዎን በአንደበታችን ፍቅርን የምንሰብክ በልባችን ግን የጥላቻ ሰይፍን የምንስል ለበቀልና ለመለያየት ሰልፍ የምንወጣ ከሆንን በአንድነት ስም ተለያይተናል፣ አብረን ያለን ቢመስለንም ላንገኛኝ ተራርቀናል፤ እናም ከያኒው ይህ ጽኑ የሆነ እውነተኛ ፍቅር በመንግሥታት፣ በመሪዎቻችን፣  በፖለቲከኞቻችን፣ በፓርቲዎች፣ በሃይማኖት አባቶችና በሃይማኖቶት ተቋማቶች፣ በቤተሰብ፣ በትዳርና በወዳጆችመካከል በቃል ወይም በፊርማ ብቻ ሳይሆን በእውነት የተግባር ቃል የጸና የፍቅር ውል ኪዳን ከሌለው ተለያይተናል ተራርቀናል ስለዚህም በዚህ ፍጹም ፍቅር ጥማት ነፍሱ የታመመችና የምታቃስት የከያኒው ነፍስ፡-
ስለ መውደድ/ሰለ ፍቅር ካልኩኝ ደከመኝ
ያኔ
ገና ውስጤን አመመኝ
እኔን
አመመኝ
አመመኝ…  አመመኝ…  አመመኝ  
በማለት የፍቅርን ህመሙን እንታመም የፍቅር ሽክሙን እንሸከም ዘንድ ይጣራልበፍቅር ኤሎሄውህብረት ይኑረን፣ በይቅርታ መንፈስ- በፍቅር እጅ ለእጅ እንያያዝ በሚል በተጣራው በትናንትናው የፍቅር ጥሪው ዛሬም ያንኑ የፍቅር አዋጅ ‹‹ስማ የሰማህ ለሰማ አሰማ›› በሚል እየጮኸ ይመስለኛልስለ ፍቅር በሚለው ጥኡም ዜማውቴዎድሮስ ካሣሁን…!!!
ረጅም እድሜ ለፍቅር!
ሰላም! ሻሎም!