Thursday, March 29, 2012

ፖፕ ሺኖዳ ሳልሳዊ አረፉ!

የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ ሆነው ከ1971(እ ኤ አ) ጀምሮ በማገልገል ላይ የነበሩት ፖፕ ሺኖዳ ሳልሳዊ በፕሮስቴት ካንሰር፣ በጉበትና ሳንባ በሽታ ለዓመታት ሲሰቃዩ ቆይተው በተወለዱ በ88 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ፖፕ ሺኖዳፖፕ ሲኖዳ በኮፕት ክርስቲያን ልጆቻቸው ዘንድ እጅግ በጣም ተወዳጅና ተፈቃሪ የነበሩ ሲሆን በበሽታ እየተሰቃዩ ከወንጌል አስተምህሮ ሳይለዩ፣ ቅዳሴ ሳያቋርጡ፣ በሐዋርያው ጉብኝቶቻቸው፣ አድባራትና ገዳማቶቻቸውን በማጽናናት ሌሊትና ቀን ደክመው አገልግሎታቸውን ለግብጽ ቤተክርስቲያን በትጋት ፈጽመው ያለፉ ታላቅ አባት ነበሩ። «ባባ ሹኑዳ» እያሉ የሚጠሯቸው ልጆቻቸው አስተምህሮአቸውን ለመስማት ሲሽቀዳደሙ፣እግሮቻቸውን፣ እጆቻቸውን ለመሳለም ሲሰለፉ ማየት እንግዳ ነገር አይደለም። ይህ ሁሉ ለክርስቶስ ቤተክርስቲያን የተሰለፉበትን አባታዊ ተልእኰ በመፈጸም እድሜአቸውን ሙሉ ባበረከቱት ትጋት የተነሳ የተሰጣቸው ትልቅ ክብር እንጂ ለውዳሴ ከንቱ እንዳልሆነ ሁላችንም የምንመሰክረው ሐቅ ነው። በአንድ ወቅት በቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን ሥርዓተ ቅዳሴ ላይ ትምህርተ ወንጌል አስተምረው የተናገሩትና እሳቸው አልቅሰው ምእመናኑን ሁሉ ያስለቀሱት መቼም አይረሳም።
እንዲህ አሉ! «ልጆቼ ካስተማርኳችሁ ሁሉ ያልነገርኳችሁ ብዙ ነገር በልቤ ውስጥ አለ፣ እሱን ለእናንተ አልነግርም ፣ የልቤን ለሚያውቅ ለኢየሱስ ለክርስቶስ ትቼዋለሁ» ሲሉ ቁጭ ባሉበት ስቅስቅ ብለው አለቀሱ።ቤተክርስቲያኑን የሞላው ሕዝብ ተከትሎ አለቀሰ። ቅዳሴውን በቀጥታ ስርጭት ይከታተል የነበረው ሁሉ በየቤቱ አነባ። አዎ ፓትርያርኩ ብዙ ምስጢራቸውን፣ችግራቸውንና ስለቤተክርስቲያን ያላቸውን ጭንቀት የመፍትሄ ባለቤት ለሆነው ለክርስቶስ ይነግሩ ነበር። በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚያቀርቧቸው ሃሳቦቻቸው መካከል «ክርስቶስ የሰጠን አንዲቱን ቤተክርስቲያን ሆኖ ሳለ እኛ ተለያይተን እንዴት ክርስቶስን በእውነት እናመልካለን፣ ክርስቶስን ይህን እያየ ዝም የሚለው እስከመቼ ነው?» እያለ እለት እለት የሚያሳስባቸውን የቤተክርስቲያን ጉዳይ የሚያነሱ ባለትልቅ ራእይ አባት ነበሩ።
 የሕይወት ታሪካቸው እንደሚያሳየው ፖፕ ሺኖዳ የቀድሞ ስማቸው «ናዚር ጋየድ ሩፋኤል» ይባል ነበር። በላዕላይ ግብጽ ፣ አስዩት አውራጃ ነሀሴ 3 ቀን 1923 ዓ /ም ተወለዱ። ከእናትና ከአባታቸው ከተወለዱት 8 ልጆቻቸው መካከል እሳቸው የመጨረሻው ልጅ ነበሩ። የ16 ዓመት እድሜአቸውን ሳያጠናቅቁ የወጣቱ ጋየድ ወላጅ እናት ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
በሰሜን የኤልሳሄል፣ በምሥራቅ ከሻራቢያ፣ በምእራብ የኤልፋራግ ክፍለ ከተሞች በሚያዋስኗት የባቡር መንደር በሆነች ው «ሹብራ»  በካይሮ ከተማ ቅዱስ እንጦንስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ወጣቱ ናዚር ጋየድ አገልግሎታቸውን ጀመሩ። ከዚያም የሰንበት ት/ቤቱ አስተማሪ ሆነው ተሾሙ። እንደገናም በማህሻማ ቅድስት ማርያም  ቤክርስቲያን ውስጥም ተዛውረው አገልግለዋል።
የበለጠ እውቀት ለመገብየት ወደካይሮ ዩኒቨርሲቲ በማቅናት በታሪክ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን ከያዙ በኋላ እዚያው ካይሮ ከተማ ውስጥ በ2ኛ ደረጃ ት/ቤት ውስጥ የእንግሊዝኛ ቋንቋና የማኅበራዊ ጥናት መምህር ሆነው ተቀጠሩ።  በ2ኛ ደረጃ ት/ቤት መምህርነት እያገለገሉ ሳለ በማታው ክፍለ ጊዜ ደግሞ በኮፕቲክ ቲኦሎጂካል ኮሌጅ በመማር የመጀመሪያ ድግሪያቸው በነገረ መለኰት ትምህርት በ1949 ዓ/ም አገኙ። ያን ጊዜ የ2ኛ ደረጃ መምህርነታቸውን ትተው እዚያው በተመረቁበት ኮሌጅ የአዲስ ኪዳን መምህር ሆነው ተቀጠሩ። እስከ 1954 ዓ/ድረስ በመንፈሳዊ ኮሌጁ መምህርነት ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ ሥራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው በመልቀቅ ሁሉ ነገር ይቅርብኝ ብለው ወደ ገዳም አመሩ። ነሐሴ 5 ቀን 1954 ዓ/ም በግብጽ ከሚገኘው የሶሪያ ገዳም ከገቡ በኋላ ዓለማዊ ስማቸው ተቀይሮ «አንቶንዮስ ኤል ሲሪያኒ» ተብለው ተጠሩ። ትርጉሙም «ሶሪያዊው እንጦንስ» ማለት ነው።
በገዳሙ ውስጥ ለሁለት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ ገዳሙ ራሳቸውን ለክርስቶስ ሙሽራ አድርገው ያጩትን እኚህን አባት ምንኩስናና ማእረገ ቅስና እንዲያገኙ አድርጓቸዋል። ከማኅበር ኑሮ ይልቅ ለብቻቸው በመለየት ስለነገረ መስቀሉ ማሰላሰል እንደሚሻል በማሰብ ለሰባት ዓመታት በጾምና በጸሎት  ተወስነው  በበዓት ውስጥ ቆይተዋል። በ1959 ዓ/ም የፓትርያርክ ምርጫ ሲደረግ የአሁኑ አባ ሺኖዳ የቀድሞው እንጦንዮስ ኤልሲሪያ ከዘጉበት ዋሻ በገዳሙ ማኅበረ መነኰሳት ተጠርተው እንዲመጡ ከተደረገ በኋላ የግብጽ ገዳማት ሁሉ የየራሳቸውን እጩ ለፓትርያርክነት ከሚያቀርቧቸው  መካከል እሳቸው ደግሞ ገዳማቸውን ወክለው እንዲወዳደሩ ተደርጎ  በውድድሩ እሳቸው ሳያልፉ ቀሩ። አብረዋቸው ከተወዳደሩት መካከል «ቄርሎስ 6ኛ» ፓትርያርክ ሆነው ተመረጡ። አባ እንጦንስ(ሺኖዳ) ወደገዳማቸው ተመልሰው ወደቀድሞ በዓታቸውና የብቸኝነት ጸሎታቸው ገቡ። ቀድሞውኑ አባ እንጦንስን ገዳሙ ወክሏቸው እንጂ ሥራቸውንና የከተማ ደመወዛቸውን እርግፍ አድርገው የተዉት ፓትርያርክ  ለመሆን በመመኘት አልነበረምና ወደበዓታቸው በመመለስ የክርስቶስን ፍቅር፣ ሞትና ትንሳዔ እንዲሁም የቅዱሳት መጻሕፍትን ምስጢር በመመርመር ተጠመዱ። የሚገርመው ደግሞ አባ እንጦንስ ለውድድር ተልከው ከ5 ተወዳዳሪዎች መካከል በውድድሩ እጣ አሸንፈው ፓትርያርክ የሆኑት ቄርሎስ 6ኛ በተሾሙ በ3ኛው ዓመት አባ እንጦንስ(ሺኖዳን) በአስቸኳይ እንዲመጡ ለገዳማቸው ትእዛዝ አስተላለፉ። አባ እንጦንስም የፓትርያርኩን ትእዛዝ አክብረው በ1962 ዓ/ም ወደ ካይሮ አመሩ። ከዚያም በፓትርያርኩ እጅ  የጵጵስና ማእረግን አባ ሺኖዳ ተብለው ተቀበሉ።
ምንም ሳይታሰብ ጳጳስ ተብለው ከተሾሙ በኋላ በጵጵስና ማእረግ የኮፕት አብያተክርስቲያናት መንፈሳዊ ኮሌጆች የበላይ ኃላፊና ዲን ሆነው ተመደቡ። አዲሱ ጳጳስ ሺኖዳም መንፈሳዊ ኰሌጆችን የሚመሩና የሚያስተምሩ መምህራንን በብቃትና በጥራት አደራጅተው በዓመት ውስጥ ቀድሞ ከነበረው ሦስት እጥፍ ተማሪዎችንና ምሩቃንን ማፍራት ቻሉ። የተንዛዛውን የቢሮክራሲ አሰራር በማሻሻልና አስተምህሮው ሁሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊውን መሠረት ብቻ የተከተለ እንዲሆንና ታሪክ፣ባህልና ትውፊት ጠቃሚ ቢሆንም የወንጌል አገልግሎትን ስለማይወክል ወጣቱ እንዲነቃቃ፣ ትውፊቱን እንደያዘ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያነብ፣ እንዲመረምር፣ እንዲማር በማድረግ የኮፕት ቤተክርስቲያንን የአዲስ ኪዳንን ትምህርታዊ አብርሆት አሳይተዋል። በዚህም የተነሳ ከቤተክርስቲያን እየራቀና በዓለማዊው ትምህርት እየተጠመደ የነበረውን ወጣት ስለቤተክርስቲያን እንዲመለከት፣ የነፍሱን ቤዛ ክርስቶስን ችላ እንዳይል በማድረጋቸው የሚመጣ የወጣቱ ቁጥር በመጨመሩ መንፈሳዊ ኰሌጆች እንዲከፈቱ፣ በተጓዳኝም ዘመናዊ ት/ቤቶች እንዲስፋፉ አድርገዋል።
በጳጳስ ሺኖዳ በኩል በግብጽ  ቤተክርስቲያን ውስጥ መነቃቃትን የፈጠረው አዲስ ትንሳዔ ብዙ ሺህ ወጣቶችን ለመሳብ፣ገዳማትና አድባራት በወንጌል መምህራንና ተማሪዎች እንዲስፋፋ አስችሏል። በዚህ የተነሳ አባ ሺኖዳ ተከታዮቻቸው በመብዛታቸውና የወንጌል መምህራችን የሚለው ሰው ቁጥር በማየሉ የተነሳ ፖፕ ቄርሎስ 6ኛን ደስ አላሰኛቸውም። እንዲያውም ይባስ ብለው ከነበሩበት የሥራ ኃላፊነት በማባረር አባ ሺኖዳ እጃቸውን አጣጥፈው እንዲቀመጡ አደረጓቸው።
የወጣቱን ልብ በወንጌል አገልግሎት መሳብ የቻሉት አባ ሺኖዳ ምንም ቅር ሳይሰኙ በፓትርያርኩ ትእዛዝ  አርፈው  ተቀምጠው ሳሉ ወጣቱ ግን አድራጎቱን በመቃወም  የቤተክርስቲያን አስተዳደር ተሐድሶ ሊደረግበት ይገባል ሲል ተቃውሞውን አሰማ። ተቃውሞው ሰፊና ሁሉን ያዳረሰ በመሆኑ በ1967 ዓ/ም መጀመሪያ አካባቢ ውዝግቡ በስምምነት ተፈጽሞ ፓትርያርኩ እግዳቸውን አንስተው አባ ሺኖዳ ወደቀደመ ሥራቸው እንዲመለሱ ተደረገ።
ከ4 ዓመታት በኋላ በ1971 ዓ/ ም ፓትርያርክ ቄርሎስ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። የፓትርያርክ ቄርሎስን ሞት ተከትሎ በ9ኛው ወር የሚተካቸው ፓትርያርክ ምርጫ ተደረገ። ለፓትርያርክ እጩነት ከቀረቡት መካከል አባ ሺኖዳ ቀድሞ የገዳም መነኩሴ እንደነበሩ በተወዳደሩበት ሁኔታ እንደገና ጳጳስ ከሆኑ በኋላም ለሁለተኛ ጊዜ ለፓትርያርክነት ውድድር ቀረቡ። ለእጩነት ከቀረቡት 5 ተወዳዳሪዎች መካከል ስማቸው ተጽፎ ከተቀመጠበት ሳጥን ውስጥ ዓይኑን በጨርቅ የተሸፈነ ልጅ አንዱን እንዲያነሳ ተደርጎ ሲገለጥ «አባ ሺኖዳ» የሚል ሆኖ ተገኘ። በዚህም ባሳደዷቸው በፓትርያርኩ ቦታ 117ኛው የኮፕት ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ሺኖዳ ሳልሳዊ ተብለው ተሾሙ። እዚህ ላይ ሳንገልጽ የማናልፈው ድንቅ ነገር በኮፕት ቤተክርስቲያን የመጨረሻ አምስት እጩ ፓትርያርኮች ላይ የድምጽ ካርድ መስጠትና የድምጽ ቆጠራ ቆጠራ ብሎ ነገር የለም።  በምእመናን፣ በመነኮሳት፣ በገዳማት፣ አድባራትና የሲኖዶስ አባላት 1000 ያህል ተወካዮች ከሚያቀርቧቸው ተጠቋሚዎች ውስጥ በድምጽ ብልጫ ያገኙ አምስት ጳጳሳት መካከል ስማቸው በወረቀት ላይ ተጽፎ በሳጥን ውስጥ ከገባ በኋላ እድሜው ከ7 ዓመት ያልበለጠ ልጅ ዓይኑን በጨርቅ ታስሮ ሲያበቃ ሳጥኑ ውስጥ ካለው እጣ አንዱን እንዲያወጣ ይደረጋል። የወጣለት እጩ ፓትርያርክ ይሆናል። ከዚያ ውጪ የምርጫ ካርድ ይዞ፤ ቡድንና ደጋፊ አስርጎ በማስገባት በሚደረግለት ፖለቲካዊ ድጋፍ እየታገዘ ፓትርያርክ ሆነ እንደሚባለው እንደሌሎቹ አብያተክርስቲያናት የማጭበርበሪያ ስልት ኮፕቶች የላቸውም።
ፖፕ ሺኖዳ ሳልሳዊ በሥራቸው ላይ ሳሉ ከፕሬዚዳንት አንዋር ሳዳት አስተዳደር ጋር ባለመስማማታቸው ሳዳት እሳቸውንና 8 ሌሎች ጳጳሳትን ከስልጣን አባሮ ጭው ካለው በረሃ በሚገኘው አባ ብሶይ ገዳም ተዘግተው እንዲቀመጡ አደረገ። በምትካቸው 5 ጳጳሳት ያለው የፓትርያርክ ወኪል የጳጳሳትን ቡድን እራሱ ሳዳት ለቤተክርስቲያኒቱ ሾመ። ቅዱስ ሲኖዶስ ድርጊቱን ተቃወመ፤ ጳጳሳቱም ሹመቱን አንቀበልም አሉ። ሲኖዶሱ የቤተክርስቲያኒቱን ሥራ ተረክቦ እስከ1984 ዓ/ም ድረስ ቆየ። አንዋር ሳዳትም በነፍሰ ገዳዮች ጥይት ተገደለ። በምትኩም ሆስኒ ሙባረክ ፕሬዚዳንት ሆኖ ሲሾም የአባ ሺኖዳም ስደት አከተመና ወደመንበራቸው በ1985 ዓ/ም ተመለሱ።
አባ ሺኖዳ ወደመንበራቸው ከተመለሱ በኋላ የወንጌል አባትነታቸውን ቀጥለዋል። በዚህም ከ100 መጻሕፍትን በላይ በአረቢኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋ ጽፈዋል። በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ፣ በመጽሔቶችና በጋዜጦች ሁሉ ወንጌልን ሰብከዋል። ነገረ ወንጌሉን አዳርሰዋል።
መዳን በማንም እንደሌለ አጥብቀው በአዳባባይ መስክረዋል። ባህሉንና ትውፊቱን እንዲጠብቅ ግን በዚያው ላይ ሙጭጭ ብሎ ወንጌልን ወደዳር የመግፋቱን ተግባር በጹኑ ተከላክለዋል። የዘመኑን ወጣት ልብ ለክርስቶስ እንዲገዛ በማድረግ ጥበብ የተሞላበትን አስተምህሮ አስፋፍተዋል። ይህንን ሁሉ ተጋድሎ ፈጽመው በተወለዱ በ88 ዓመታቸው፣ በተሾሙ 41 ዓመታቸው ከዚህ ከሚያልፈው ዓለም ወደማያልፈው ዓለም በመጋቢት 17/2012 ዓ/ም ሄደዋል። እኒህን የወንጌል መምህር፣ ዘመኑን የዋጁ፤ ራሳቸውን በንጽህና የክርስቶስ ሙሽራ አድርገው ያቀረቡ አባት ነፍስ ከቅዱሳኖቹ እንዲደምርልን ለወንጌሉ አገልግሎት ዘመናቸውን ሁሉ በመስጠት የተጋደሉለት ክርስቶስን እንለምነዋለን። አሜን።
(ተጨማሪ፤ በአጽዋማት ጊዜ በበዓላት ቀን ሥርዓተ ቅዳሴ ጥዋት እንዲሆን ያደረጉት ፖፕ ሺኖዳ ናቸው። ለምሳሌ  የእመቤታችን ወርሃዊው በዓል 21ኛው ቀን ከሰኞ እስከ ዓርብ ቢውል በጾመ አርብዓ ይሁን በጾመ ፍልሰታ ቅዳሴ የሚቀደሰው ጥዋት እንጂ እንደኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ውሎ ከሰዓት በኋላ አይደለም። ይህን ያደረጉት ይህ ቀኖና እንጂ ዶግማ ባለመሆኑ ሕዝቡ ከማስቀደስ እንዳይርቅ፣ ለኑሮው ደፋ ቀና የሚለው ምእመን  በድካም የተነሳ በመሰላቸት ወጥቶ እንዳይቀር፤ ሙሉ ቀን ጾሙን፣ ሥራውንና ቅዳሴውን ለመተግበር ስለሚቸገር ያሻሻሉበት ዋና ምክንያት ነው። ሥርዓቱን ያሻሻሉ አባት ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ ቢሆን ኖሮ ተሀድሶ ተብለው ይደበደቡ ነበር። ደግነቱ እሳቸው የኮፕት ፓትርያርክ ናቸው።)
(በጽሁፋችን ውስጥ የተጠቀሱት ዓ/ምህረቶች ሁሉ እንደአውሮፓውያን አቆጣጠር ነው)

Wednesday, March 28, 2012

በጋሸ ስብሐት ስም ቤተ መፅሕፍት ሊከፈት ነው




  በቅርቡ ከዚህ አለም በሞት በተለየው በደራሲ  ገ/አግዚአብሔር ስም ቤተ መፅሐፍት ለማቋቋም አንደታሰበ ተሰማ::
 በስብሐት ጓደኞች ክበብ አባላት ይከፈታል የተባለው ቤተ መፅሀፍት የጋሽ ስብሀት ምፅሀፍት የጋዜጣና የመፅሄት መጣጥፎችን ጨምሮ የልዩ ልዩ ደራስያን ጋዜጠኞችን ስራ ለአንባቢያን እንደሚያቀርቡ የክበቡ አስተባባሪ አርቲስት ፈለቀ አበበ ገልፀዋል፡፡
     ቤተ መፅሀፍቱ መቼና የት እንደሚከፈት የተጠየቀው አርቲስት ፈለቀ አበበ በቅርቡ ሚያዝያ ፯ቀን ፪፻፬ በሚከበረው የልደት በዓሉ ይፋ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

for more information visit
on face book

Tuesday, March 27, 2012

16 ሰዎች የጨፈጨፈው የአሜሪካ ኮማንዶ ወታደር

16 ሰዎች የጨፈጨፈው የአሜሪካ ኮማንዶ ወታደር አፍጋኒስታን ሕዝብ በጦርነት ውስጥ መኖርን ወይም የጥይት ድምፅን እንደ ነፃነት ወግ ማዳመጡን የሕይወቱ አንድ አካል አድርጎ መጓዝ ከጀመረ እነሆ ከአሥር ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል፡፡በቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት፣ በኋላም በአሜሪካና በኔቶ መራሹ “ሰላም አስከባሪ” ስም በዘመን አመጣሹ የመሣርያ ዓይነት የምትቀጠቀጠው አፍጋኒስታን፣ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ደግሞ ስለአስከፊነቱ በአፍጋኒስታን ፕሬዚዳንት “ይቅርታ የማይደረግለት” የተባለ ጭፍጨፋ ተፈጽሞባታል፡፡ Image
ወትሮውንም ሞት ብርቃቸው ላልሆኑት የአፍጋኒስታን ዜጎች በአጥፍቶ ጠፊዎች የቦምብ ጥቃት ሲታመሱ፣ በጦርነት መሃል ሲቪሎች ሁሌም ማለቃቸው የተለመደ ነው፡፡ የሰሞኑን ለየት ያደረገው ምንም ዓይነት የጦርነት ድባብ ባልነበረበት ሥፍራ ሕፃናትና ሴቶችን ጨምሮ 16 ሰላማዊ ሰዎች መሞታቸው ነው፡፡ ከሟቾቹ መካከል የተወሰኑት በአካላቸው ላይ ቃጠሎ መድረሱ ተነግሯል፡፡ የግድያው አፈጻጸም ይቅርታ የማይኖረው ደግሞ አንድ የአሜሪካ ወታደር ቤት ለቤት እያሰሰ የፈጸመው ፍጅት በመሆኑ፣ ጉዳዩ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን ጨምሮ የኔቶንና የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣናትን ያስደነገጠ ሆኗል፡፡

ባለሥልጣናቱ ጉዳዩ ይመረመራል፣ ለፍርድ ይቀርባል እያሉ ባሉበትና የአፍጋኒስታን ዜጎች የተቃውሞ ሠልፍ እየወጡ በሚታዩበት ወቅት፣ 16 ሲቪሎችን ለሕልፈተ ሕይወት የዳረገው የአሜሪካ ወታደር ከባልደረቦቹ የተገለለና የአዕምሮ ችግር ያለበት ስለመሆኑ፣ ወታደራዊ የአዕምሮ ጤና ስፔሻሊስቶች እያስታወቁ ነው፡፡ ወታደሩ ቀደም ሲል በኢራቅ ለሦስት ዓመታት ያህል ማገልገሉን፣ ደቡብ አፍጋኒስታን ወደ ምትገኘው ካንዳሃር ከተማ የተላከውም በዚሁ የሚገኘውንና አነስተኛ ቁጥር ያለውን የአሜሪካ ወታደራዊ ቡድን ለመርዳት እንደሆነ የአፍጋኒስታንና የፔንታጎን ባለሥልጣናት የጉዳዩን የኋላ ታሪክ አስመልክተው ባወጡት መግለጫ አመላክተዋል፡፡

ለአሜሪካ ተዋጊ ኃይሎች ካለፉት አሥር ዓመታት ጀምሮ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት የሥነ አዕምሮ ሐኪሙ ዶክተር ጆናታን ሻያ እንደገለጹት፣ ወታደሩ የፈጸመው ድርጊት ልብ የሚነካና አሳዛኝ ሲሆን፣ በ20 ዓመታት ታሪክ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ድርጊት የፈጸሙ የአዕምሮ ሕሙማንም ሁለት ብቻ ናቸው፡፡

ሲኤንኤን እንደዘገበው፣ ይኼው አሜሪካዊ ወታደር ቤት ለቤት እየዞረ የፈጸመው አሰቃቂ ግድያ ፍጹም ይቅርታ የማይደረግለት ወንጀል ነው ሲሉ የአፍጋኒስታኑ ፕሬዚዳንት ሃሚድ ካርዛይ እንደተናገሩት ሁሉ፣ የኔቶ ዓለም አቀፍ የፀጥታ ድጋፍ ኃይል በበኩሉ ወታደሩ ግድያውን የፈጸመው በራሱ ተነሳሽነት ነው ብሏል፡፡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ኦባማ ግድያውን “አሳዛኝና አስደንጋጭ፤” ብለውታል፡፡ ለሟች ቤተሰቦችና ለመላው የአፍጋኒስታን ሕዝብ የተሰማቸውን ሐዘን ለፕሬዚዳንት ሃሚድ ካርዛይ በስልክ አስተላልፈዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ካርዛይ ከቢሮአቸው በሰጡት መግለጫ ግድያው የተፈጸመው ከካንዳሃር 25 ኪሎ ሜትር ወጣ ብሎ በሚገኘው ልዩ ስሙ “ፓንጃዊ” ተብሎ በሚጠራ ሥፍራ ነው፡፡ የግዛቱ ምክር ቤት አባል ለሲኤንኤን እንደተናገሩት፣ ወታደሩ ግድያውን የፈጸመው ተቀራርበው በሚገኙ መንደሮች ውስጥ ባሉ አራት መኖርያ ቤቶች ውስጥ ነው፡፡ ከተገደሉት ንጹኃን ዜጎች መካከልም አራት ወንዶች፣ ሦስት ሴቶችና ዘጠኝ ሕፃናት ይገኙበታል፡፡ ሌሎች አምስት ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል፡፡ የዓለም ዓቀፉ የፀጥታና ድጋፍ ኃይል ቃል አቀባይ ካፒቴን ደስቲን ግድያው በኔቶና በአፍጋኒስታን ባለሥልጣናት አማካይነት እየተጣራ መሆኑን፣ ግድያው የተፈጸመበት አካባቢ ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነፃ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡

በካንዳሃር ግዛት የተፈጸመው ግድያ በአሜሪካና በአፍጋኒስታን መካከል ያለውን ግንኙነት ጥላ ሊያጠላበት እንደሚችል ፕሬዚዳንት ኦባማ ስጋታቸውን ሲገልጹ፣ የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ሊዮን ፓኔታ ደግሞ ተጠርጣሪው ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ የሞት ቅጣት እንደሚጠብቀው ተናግረዋል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ጉዳዩ የሚታየው በዩናይትድ ስቴትስ ወታደራዊ ፍርድ ቤት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ወታደሩ ድርጊቱን ከፈጸመ በኋላ እጁን በሰላም መስጠቱ ከጥፋቱ መጸጸቱን ለመግለጽ አይመስልዎትም ወይ? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄም፣ “እኔም እንደዚያ ይመስለኛል፤” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በአፍጋኒስታን የተፈጸመውን ጭፍጨፋ በመቃወም ትናንት 600 የሚጠጉ ተማሪዎች በጃላላባድ ከተማ ሰላማዊ ሠልፍ በማካሄድ ጥቃቱን ከማውገዛቸውም በላይ፣ በከፍተኛ ድምፅ “ሞት ለአሜሪካ፣ ሞት ለኦባማ” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ በካንዳሃር የተቃውሞ ሠልፍ ሲካሄድ ከዚህ ባሻገር “ጨካኝ አረመኔ” ባሏቸው የአሜሪካ ወታደሮች ላይ ብቀላ ለመፈጸም መዘጋጀታቸውን ታሊባኖች እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡ በትናንትናው ዕለት የሟቾች ቀብር ሲፈጸም በአሜሪካ ላይ ከፍተኛ ውግዘት ተደርጓል፡፡ ታሊባኖች በወቅቱ ተኩስ መክፈታቸውም ተሰምቷል፡፡

አፍጋኒስታን ውስጥ ከሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮች መካከል አብዛኞቹ እ.ኤ.አ. በ2014 ለቅቀው እንደሚወጡ ፕሬዚዳንት ኦባማ ቢያስታውቁም፣ ዓለም አቀፉ ኃይል ከአፍጋኒስታን ለቅቆ የሚወጣው በጥድፊያ ሳይሆን በተረጋጋና ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ እንደሆነ በመግለጽ የመወጣቱ ሒደት ሊዘገይ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡

የቢቢሲ ተንታኞች እንደገለጹት፣ በአደጋው ሳቢያ ፕሬዚዳንት ሃሚድ ካርዛይ ችግር ውስጥ ገብተዋል፡፡ ምክንያቱም የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ከመሆናቸውም ባሻገር የካንዳሃር የጎሳ መሪ ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ ለሟች ቤተሰቦች ግድያውን አስመልክተው ማብራራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ አፍጋኒስታናውያን የወታደሩ ጉዳይ በአፍጋኒስታን ፍርድ ቤት እንዲታይ ይፈልጋሉ፡፡ ይሁን እንጂ የኔቶ አባል አገሮች ወታደሮች ለሚፈጽሙት ሕገወጥ ተግባር በአገራቸው እንዲዳኙ የሚያስገድደውን ስምምነት ካቡል፣ ከዋሽንግተንና ከኔቶ አባል አገሮች ጋር ቀደም ብላ ተፈራርማለች፡፡

በዚህ የተነሳ በአሜሪካ የሚካሄደው የክስ ሒደት በግልጽና ጋዜጠኞች ባሉበት እንዲታይ፣ ክሱም ከሳምንታት ወይም ከወራት በኋላ እንዲጀመር ካቡል ግፊት እንደምታደርግ የአፍጋኒስታን ፕሬዚዳንት ረዳት መናገራቸው ታውቋል፡፡ 

https://www.facebook.com/tarikuasefa

Monday, March 26, 2012

ሰማዕቱ ቅዱስ እስጢፋኖ

እንኳን ለሰማዕቱ ቅዱስ እስጢፋኖ ወርሃዊ መታሰቢያ በዓል አደረሳችሁ!!!
+++ሰው ግን ዓለምን ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢጎዳ ምን ይረባዋል/ምን ይጠቅመዋል?+++ ማቴ.፲፮፡፳፮
የቅዱሳኑ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው። መዝ. 115/116፡15
+++እኔን የሚወድ ቢኖር እራሱን ይካድ መስቀሌንም ተሸክሞ /መከራዬን ሳይሰለች/ ዕለት ዕለት ይከተለኝ+++፡፡ ማቴ ፲፡፴፰-፵፪+++ስለ ጽድቅ የሚራቡና የሚጠሙ፣ እንዲሁም የሚሰደዱ ብጹዓን ይጠግባሉና፣ መጽናናትንም ያገኛሉና…+++ ጌታ በተራራ ስብከቱ ከተናገራቸው፣ ካስተማራቸው የሕይወት ምግብ የሆነ ቃሉ ማቴ.፭፡፩-ፍጻሜ
ቅዱስ እስጢፋኖስ በፍርድ አደባባይ ሲቆምና ሲከሠስ እውነቱን መናገሩ ሕይወቱን እንደሚያስከፍለው እያውቀ፡፡ እውነቱን መናገር አልፈራም፡፡ አያችሁ ቅዱስ እስጢፋኖስ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ነበር ያስተዋለው፡፡ ውጤቱ ምንም ይሁን፡፡ እግዚአብሔር በእውነት የተሞላን እንድንሆን ይፈልጋል፡፡ የክርስቶስ ምስክር ሆነው የተሰዉት ቅዱሳን የክብር አክሊል የተቀዳጁት ለእውነት ስለሞቱ ነው፡፡ ነገር ግን በመንፈስ ሕያዋን ናቸው፡፡ በዘላለማዊ ደስታም ከእግዚአብሔር ጋር ኖረዋል፡፡
እስጢፋኖስም ጸጋንና ኃይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅንና ታላቅ ምልክትን ያደርግ ነበር። የነፃ ወጪዎች ከተባለችው ምኵራብም ከቀሬናና ከእስክንድርያም ሰዎች ከኪልቅያና ከእስያም ከነበሩት አንዳንዶቹ ተነሥተው እስጢፋኖስን ይከራከሩት ነበር፤ ይናገርበት የነበረውንም ጥበብና መንፈስ ይቃወሙ ዘንድ አልቻሉም። በዚያን ጊዜ። በሙሴ ላይ በእግዚአብሔርም ላይ የስድብን ነገር ሲናገር ሰምተነዋል የሚሉ ሰዎችን አስነሡ። ሕዝቡንና ሽማግሌዎችንም ጻፎችንም አናደዱ፥ ቀርበውም ያዙት ወደ ሸንጎም አመጡትና። ይህ ሰው በዚህ በተቀደሰው ስፍራ በሕግም ላይ የስድብን ነገር ለመናገር አይተውም፤ ይህ የናዝሬቱ ኢየሱስ ይህን ስፍራ ያፈርሰዋል ሙሴም ያስተላለፈልንን ሥርዓት ይለውጣል ሲል ሰምተነዋልና የሚሉ የሐሰት ምስክሮችን አቆሙ። በሸንጎም የተቀመጡት ሁሉ ትኵር ብለው ሲመለከቱት እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ፊቱን አዩት። ፮፡፰-፲፭)
“ይህ እንዴት ያለ ይቅርታ ነው? ልክ ጌታ በዚያ በመከራ ሰዓት ብዙ መከራ ሲያጸኑበት አባት ሆይ የሚያደርጉት አያቁምና የቅር በላቸው ብሎ የፍቅር አምላክ ይቅርታ እንዳደረገላቸው ሁላ የጌታው ተከታይ የሆነው፤ እስጢፋኖስም።”
“ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ነፍሴን ተቀበል ብሎ ሲጠራ ይወግሩት ነበር። ተንበርክኮም። ጌታ ሆይ፥ ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህንም ብሎ አንቀላፋ። ሳውልም በእርሱ መገደል ተስማምቶ ነበር።” (የሐዋ.ሥራ ፯፡፶፱-፷)



የሰማዕቱ በረከት ይደርብን እስከ ሞት ድረስ ለአምላካችን እንድንታመን እርሱ ይርዳን፡፡ እስከ መጨረሻ ድረስ የታመንህ ሁን የህይወት አክሊል እሰጣሃለሁ ራዕይ 2፡10 ለዚህ ነው እኮ ቅ/ጳውሎስ “እሩጫዬን ጨርሻለሁ ሃይማኖቴን ጠብቄያለሁ ከእንግዲህ የሕይወት አክሊል ይጠብቀኛል” ያለው ፪ጢሞ.፬፡፮-፯
W የእግዚአብሔር፣ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት፣ የቅዱሳን አበው መነኮሳት፣ የቅዱሳት አንስት፣ የደናግላንና የቅዱሳን ሁሉ ምልጃና ቃል-ኪዳናቸው ባለንበት ከሁላችን ጋር ይሁን ይቆየን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡ አነሳስቶ ያስጀመረኝ አስጀምሮ ያስጨረሰኝ የቅዱሳን አባቶችን አምላክ ይክበር ይመስገን አሜኝ + + m..z