Tuesday, March 27, 2012

16 ሰዎች የጨፈጨፈው የአሜሪካ ኮማንዶ ወታደር

16 ሰዎች የጨፈጨፈው የአሜሪካ ኮማንዶ ወታደር አፍጋኒስታን ሕዝብ በጦርነት ውስጥ መኖርን ወይም የጥይት ድምፅን እንደ ነፃነት ወግ ማዳመጡን የሕይወቱ አንድ አካል አድርጎ መጓዝ ከጀመረ እነሆ ከአሥር ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል፡፡በቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት፣ በኋላም በአሜሪካና በኔቶ መራሹ “ሰላም አስከባሪ” ስም በዘመን አመጣሹ የመሣርያ ዓይነት የምትቀጠቀጠው አፍጋኒስታን፣ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ደግሞ ስለአስከፊነቱ በአፍጋኒስታን ፕሬዚዳንት “ይቅርታ የማይደረግለት” የተባለ ጭፍጨፋ ተፈጽሞባታል፡፡ Image
ወትሮውንም ሞት ብርቃቸው ላልሆኑት የአፍጋኒስታን ዜጎች በአጥፍቶ ጠፊዎች የቦምብ ጥቃት ሲታመሱ፣ በጦርነት መሃል ሲቪሎች ሁሌም ማለቃቸው የተለመደ ነው፡፡ የሰሞኑን ለየት ያደረገው ምንም ዓይነት የጦርነት ድባብ ባልነበረበት ሥፍራ ሕፃናትና ሴቶችን ጨምሮ 16 ሰላማዊ ሰዎች መሞታቸው ነው፡፡ ከሟቾቹ መካከል የተወሰኑት በአካላቸው ላይ ቃጠሎ መድረሱ ተነግሯል፡፡ የግድያው አፈጻጸም ይቅርታ የማይኖረው ደግሞ አንድ የአሜሪካ ወታደር ቤት ለቤት እያሰሰ የፈጸመው ፍጅት በመሆኑ፣ ጉዳዩ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን ጨምሮ የኔቶንና የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣናትን ያስደነገጠ ሆኗል፡፡

ባለሥልጣናቱ ጉዳዩ ይመረመራል፣ ለፍርድ ይቀርባል እያሉ ባሉበትና የአፍጋኒስታን ዜጎች የተቃውሞ ሠልፍ እየወጡ በሚታዩበት ወቅት፣ 16 ሲቪሎችን ለሕልፈተ ሕይወት የዳረገው የአሜሪካ ወታደር ከባልደረቦቹ የተገለለና የአዕምሮ ችግር ያለበት ስለመሆኑ፣ ወታደራዊ የአዕምሮ ጤና ስፔሻሊስቶች እያስታወቁ ነው፡፡ ወታደሩ ቀደም ሲል በኢራቅ ለሦስት ዓመታት ያህል ማገልገሉን፣ ደቡብ አፍጋኒስታን ወደ ምትገኘው ካንዳሃር ከተማ የተላከውም በዚሁ የሚገኘውንና አነስተኛ ቁጥር ያለውን የአሜሪካ ወታደራዊ ቡድን ለመርዳት እንደሆነ የአፍጋኒስታንና የፔንታጎን ባለሥልጣናት የጉዳዩን የኋላ ታሪክ አስመልክተው ባወጡት መግለጫ አመላክተዋል፡፡

ለአሜሪካ ተዋጊ ኃይሎች ካለፉት አሥር ዓመታት ጀምሮ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት የሥነ አዕምሮ ሐኪሙ ዶክተር ጆናታን ሻያ እንደገለጹት፣ ወታደሩ የፈጸመው ድርጊት ልብ የሚነካና አሳዛኝ ሲሆን፣ በ20 ዓመታት ታሪክ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ድርጊት የፈጸሙ የአዕምሮ ሕሙማንም ሁለት ብቻ ናቸው፡፡

ሲኤንኤን እንደዘገበው፣ ይኼው አሜሪካዊ ወታደር ቤት ለቤት እየዞረ የፈጸመው አሰቃቂ ግድያ ፍጹም ይቅርታ የማይደረግለት ወንጀል ነው ሲሉ የአፍጋኒስታኑ ፕሬዚዳንት ሃሚድ ካርዛይ እንደተናገሩት ሁሉ፣ የኔቶ ዓለም አቀፍ የፀጥታ ድጋፍ ኃይል በበኩሉ ወታደሩ ግድያውን የፈጸመው በራሱ ተነሳሽነት ነው ብሏል፡፡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ኦባማ ግድያውን “አሳዛኝና አስደንጋጭ፤” ብለውታል፡፡ ለሟች ቤተሰቦችና ለመላው የአፍጋኒስታን ሕዝብ የተሰማቸውን ሐዘን ለፕሬዚዳንት ሃሚድ ካርዛይ በስልክ አስተላልፈዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ካርዛይ ከቢሮአቸው በሰጡት መግለጫ ግድያው የተፈጸመው ከካንዳሃር 25 ኪሎ ሜትር ወጣ ብሎ በሚገኘው ልዩ ስሙ “ፓንጃዊ” ተብሎ በሚጠራ ሥፍራ ነው፡፡ የግዛቱ ምክር ቤት አባል ለሲኤንኤን እንደተናገሩት፣ ወታደሩ ግድያውን የፈጸመው ተቀራርበው በሚገኙ መንደሮች ውስጥ ባሉ አራት መኖርያ ቤቶች ውስጥ ነው፡፡ ከተገደሉት ንጹኃን ዜጎች መካከልም አራት ወንዶች፣ ሦስት ሴቶችና ዘጠኝ ሕፃናት ይገኙበታል፡፡ ሌሎች አምስት ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል፡፡ የዓለም ዓቀፉ የፀጥታና ድጋፍ ኃይል ቃል አቀባይ ካፒቴን ደስቲን ግድያው በኔቶና በአፍጋኒስታን ባለሥልጣናት አማካይነት እየተጣራ መሆኑን፣ ግድያው የተፈጸመበት አካባቢ ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነፃ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡

በካንዳሃር ግዛት የተፈጸመው ግድያ በአሜሪካና በአፍጋኒስታን መካከል ያለውን ግንኙነት ጥላ ሊያጠላበት እንደሚችል ፕሬዚዳንት ኦባማ ስጋታቸውን ሲገልጹ፣ የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ሊዮን ፓኔታ ደግሞ ተጠርጣሪው ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ የሞት ቅጣት እንደሚጠብቀው ተናግረዋል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ጉዳዩ የሚታየው በዩናይትድ ስቴትስ ወታደራዊ ፍርድ ቤት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ወታደሩ ድርጊቱን ከፈጸመ በኋላ እጁን በሰላም መስጠቱ ከጥፋቱ መጸጸቱን ለመግለጽ አይመስልዎትም ወይ? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄም፣ “እኔም እንደዚያ ይመስለኛል፤” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በአፍጋኒስታን የተፈጸመውን ጭፍጨፋ በመቃወም ትናንት 600 የሚጠጉ ተማሪዎች በጃላላባድ ከተማ ሰላማዊ ሠልፍ በማካሄድ ጥቃቱን ከማውገዛቸውም በላይ፣ በከፍተኛ ድምፅ “ሞት ለአሜሪካ፣ ሞት ለኦባማ” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ በካንዳሃር የተቃውሞ ሠልፍ ሲካሄድ ከዚህ ባሻገር “ጨካኝ አረመኔ” ባሏቸው የአሜሪካ ወታደሮች ላይ ብቀላ ለመፈጸም መዘጋጀታቸውን ታሊባኖች እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡ በትናንትናው ዕለት የሟቾች ቀብር ሲፈጸም በአሜሪካ ላይ ከፍተኛ ውግዘት ተደርጓል፡፡ ታሊባኖች በወቅቱ ተኩስ መክፈታቸውም ተሰምቷል፡፡

አፍጋኒስታን ውስጥ ከሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮች መካከል አብዛኞቹ እ.ኤ.አ. በ2014 ለቅቀው እንደሚወጡ ፕሬዚዳንት ኦባማ ቢያስታውቁም፣ ዓለም አቀፉ ኃይል ከአፍጋኒስታን ለቅቆ የሚወጣው በጥድፊያ ሳይሆን በተረጋጋና ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ እንደሆነ በመግለጽ የመወጣቱ ሒደት ሊዘገይ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡

የቢቢሲ ተንታኞች እንደገለጹት፣ በአደጋው ሳቢያ ፕሬዚዳንት ሃሚድ ካርዛይ ችግር ውስጥ ገብተዋል፡፡ ምክንያቱም የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ከመሆናቸውም ባሻገር የካንዳሃር የጎሳ መሪ ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ ለሟች ቤተሰቦች ግድያውን አስመልክተው ማብራራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ አፍጋኒስታናውያን የወታደሩ ጉዳይ በአፍጋኒስታን ፍርድ ቤት እንዲታይ ይፈልጋሉ፡፡ ይሁን እንጂ የኔቶ አባል አገሮች ወታደሮች ለሚፈጽሙት ሕገወጥ ተግባር በአገራቸው እንዲዳኙ የሚያስገድደውን ስምምነት ካቡል፣ ከዋሽንግተንና ከኔቶ አባል አገሮች ጋር ቀደም ብላ ተፈራርማለች፡፡

በዚህ የተነሳ በአሜሪካ የሚካሄደው የክስ ሒደት በግልጽና ጋዜጠኞች ባሉበት እንዲታይ፣ ክሱም ከሳምንታት ወይም ከወራት በኋላ እንዲጀመር ካቡል ግፊት እንደምታደርግ የአፍጋኒስታን ፕሬዚዳንት ረዳት መናገራቸው ታውቋል፡፡ 

https://www.facebook.com/tarikuasefa

No comments:

Post a Comment