Thursday, April 19, 2012

አምስቱ ዓይነት ኢቫንጋዲ - የሐመሮች ትውፊት

www.facebook.com/tarikuasefa

(በምዕራፍ ብርሃኔ)

ኢቫንጋዲ ሐመሮች ለዘመናት ያቆዩት ባህላዊ ጭፈራቸው ነው፡፡ በቅርስ ጥናትና ባለሥልጣን በታተመ አንድ የኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርሶች ኢንቬንቶሪ እንደጠቆመው፣ ‹‹ኢባን ማለት ምሽት ማለት ሲሆን፣ ጋዲ ማለት ጭፈራ ወይም ዝላይ ማለት ነው፡፡››
ጭፈራውን የሚያደርጉት ወጣት ሴቶችና ወንዶች ሲሆኑ፣ ጭፈራው ሲጋመስ በእድሜ የገፉ ወንድና ሴቶች ለክብራቸው ተለምነው እንዲጨፍሩ ይደረጋል፡፡

ኢቫንጋዲ በአምስት ምክንያቶች ይጨፈራል፡፡ የመጀመሪያው ምክንያት እህል ሲሰበሰብ የደስታና የፌሽታ ጊዜ ስለሚሆን ሁሉም ተሰባስቦ ጭፈራው ይካሄዳል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ረሃብ ሲሆን ችግራቸውን፣ ድካማቸውንና ረሀባቸውን እንዳያስቡ ሲሉ በጭፈራው ሰውነታቸው አድክመው ለመተኛነት ይጠቀሙበታል፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ አርብቶ አደሩ ለመፎከሪያነት፣ ለማሞገሻነት የሚጠቀምበትን ቁመናውም ሆነ የቀንድ አበቃቀሉ ልዩ የሆነውን ሰንጋ በሬ እድሜው ሲገፋ፣ ጓደኞቹ እንበላለን ሲሉ ኢቫንጋዲ ይጨፈራል፡፡ ‹‹ይህ ኬንያ ጠረፍ ድረስ ወስጄ ግጦሽ አስግጬዋለሁና ጀግና በሬዬ ነው፤›› በማለት ኩራቱን የሚገልጸው አርብቶ አደር ብዙ ጥይት ተተኩሶ በሬው ሲታረድበት እሱ ሲያለቅስ፣ ጓደኞቹ ደግሞ በደስታ በመፍለቅለቅ ይበሉታል፡፡ ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ ልጃገረዶች እየጨፈሩ ወደ ሰው ቤት በመሄድ እህል ይሰበስባሉ፡፡ ወንዶች ደግሞ ቅቤ ገዝተው ያመጣሉ፡፡ ከዛ ሴቶቹ ምግቡንና መጠጡን ካስተካከሉ በኋላ ማኅበረሰቡ ተሰብስቦ ኢቫንጋዲ ይጨፍራል፡፡ አራተኛው የኢቫንጋዲ ጭፈራ የሚካሄደው ደግሞ አንድ ወንድ ሊያገባ ሲል ከስምንት እስከ አሥር የሚሆኑ ሰንጋ በሬዎች ጭራቸውና ቀንዳቸው ባላጩ ነገር ግን ለማጨት እየተዘጋጁ ባሉ ወንዶች ተወጥሮ በበሬዎቹ ጀርባ ላይ እየተረማመደ ይዘላል፡፡ ሙሽራው (እኩሌ) ዓይነ ስውር ወይም አካል ጉዳተኛ ከሆነ ከብቶች ተደርድረው በአንገታቸው ስር እንዲሾልክ ይደረግና ዘሏል ይባልለታል፡፡ እኩሌው ይህን በፈጸመ ማግሥት የኢቫንጋዲ ጭፈራ ይደረጋል፡፡

አምስተኛው ዓይነት ደግሞ ነዋሪዎቹ በጎብኚዎች ጥያቄ ኢቫንጋዲን የሚጨፍሩበት ነው፡፡ ከሚጨፍሩበት ባህላዊ ዐውድ ውጪ በመጫወታቸው፤ ክፍያ ይጠይቁበታል፡፡

የኢቫንጋዲ ጭፈራ ሲካሄድ በአካባቢው ስላለው ችግር፣ ስለጠፋ በሬ፣ ጥሩ የሳር ግጦሽና ውሃ የት እንዳለ የሚጠቋቁምበትና አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን የሚለዋወጡበት አጋጣሚ ነው፡፡

ኢቫንጋዲ ሲጨፈር ቦርዴ (ባህላዊ አልኮል መጠጥ) ይጠጣል፤ ከብት ይጣላል፤ ፍየል ይታረዳል፡፡ ሐመሮች የተጣለው ከብት ሆድ እቃ ሲዘረገፍ የሚወጣው ፈርስ ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ አካል ላይ ያለባቸውን በሽታ ይፈውሳል ብለው ስለሚያምኑ፣ ከተሰበሰበው ሰው ውስጥ ታማሚ ነኝ ያለ የበሬውን ፈርስ ይጠጣል፤ ወይንም ደግሞ ገላውን ይቀባል፡፡ በወቅቱ የተጣለው በሬ ስጋ በእንጨት ውስጥ እንዲሾልክ ተደርጎ በክብ ይደረደርና በመሃል ላይ ትልቅ ግንድ በእሳት ተለኩሶ በወላፈኑ ይጠበሳል፡፡
የተጠበሰውን ስጋ የሚበላ እንዳለ ሁሉ ጥሬ ጨጓራን የሚበሉም አይታጡም፡፡ በኢቫንጋዲ ጊዜ ዘመድ፣ ወዳጅ፣ ጎረቤትና ጓደኛ ተሰባስቦ ማውጋቱ፣ መብላቱ መጠጣቱና መጨፈሩ እጅግ ያይላል፡፡

በኢቫንጋዲ ጭፈራ ላይ በሰፊው የሚሳተፉት ወጣቶች ቢሆኑም ሽማግሌዎችና አሮጊቶች ተለምነው ለተወሰኑ ደቂቃዎች ቢጨፍሩም መድረኩን ለወጣቶቹ መልሰው ያስረክባሉ፡፡ ሁሉም የቀረበለትን ቦርዴ ስለሚጠጣ የስካር መንፈስን በስሱ ያስተናግዳል፡፡

ጭፈራው ሲጀመር ወንዶቹና ሴቶቹ ፊት ለፊት ይደረደራሉ፡፡ ወንዶቹ እየዘፈኑ ዘለል ዘለል እያሉ በክብ ሲሽከረከሩ፣ ሴቶቹም ዘለል ዘለል እያሉ ወደ ወንዶቹ በመሄድ የሚፈልጉትን ጎረምሳ በእግራቸው መታ አድርገው ይዞራሉ፡፡ ወንዱም ስለተመረጠ ከሴቷ ኋላ ኋላ እየዘለለ ይጨፍራል፡፡ እርሷም ሰውነታቸው እንዳይነካካ በሚመስል ሁኔታ እየሸሸች እና እየተዟዟረች ትጨፍራለች፡፡ ጭፈራውን ልክ ሲያሳርጉት ወንዶቹ ወደ ቦታቸው ሲሄዱ ሴቶቹም በሩጫ ወደ ቦታቸው ይመለሳሉ፡፡ ሮጣ የሄደችውን ሴት ሲያስደንሳት የነበረው ወንድ ተከትሎ ከኋላዋ በመቆም ከወገቡ ወደፊት ለመጥ፣ ከጉልበቱ ደግሞ ሰበር ብሎ መቀመጫዋን ይነካታል፡፡ ከዚያም እርሷም ትሽኮረመማለች፤ እርሱም ወደ ቦታው ይመለሳል፡፡ እንዲህ እንዲያ እያለ ጭፈራው ይቀጥላል፡፡

አብረው የሚጨፍሩት ፍቅረኛሞች ወይም ደግሞ የሚከጃጀሉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በኢቫንጋዲ ላይ  ከተገናኙ ግን ከጭፈራው በኋላ ወሲብ መፈጸማቸው አይቀሬ ነው፡፡ ወሲብን ከትዳር በፊት መፈጸም ለሐመሮች ነውር አይደለም፡፡ ወንዱም ሆነ ሴቷ ለሌላ ሰው ለመዳር የታጩ እንኳን  ቢሆኑም ወሲብን ሲፈጽሙ እጅ ከፍንጅ አይያዙ እንጂ የሚከለክላቸው ምንም አይነት ሕግ የለም፡፡
www.facebook.com/tarikuasefa 

No comments:

Post a Comment