Sunday, May 6, 2012

ምሥጢረኛው ባለቅኔ - የጸጋዬ ገብረ መድኅን ‹‹አዋሽ››




ባለቅኔውና ጸሐፌ ተውኔቱ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን (1928-1998) በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ሁነኛ ስፍራ አላቸው፡፡ በአማርኛና በእንግሊዝኛ በጻፏቸው ልጨኛ (ማስተርፒስ) ሥራዎቻቸውም ግኑን ናቸው፡፡
ከአምስት ዓመት በፊት የካቲት 18 ቀን 1998 ዓ.ም. ያረፉት ሎሬት ጸጋዬ ከጻፏቸው መጻሕፍት አንዱ ‹‹እሳት ወይ አበባ›› የሥነ ግጥም መድበል ነው፡፡

‹‹ምሥጢረኛው ባለ ቅኔ›› የተሰኘ በደራሲው ጥበባዊ ሕይወት ዙሪያ መጽሐፍ ያሳተሙት አቶ ሚካኤል ሺፈራው፣ በቅርቡ ‹‹አንድምታ ወሐተታ ዘጸጋዬ ገብረ መድኅን›› በሚል ርእስ በአንድ መድረክ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበው ነበር፡፡

በ‹‹እሳት ወይ አበባ›› መድበል ላይ ባተኮረው ጥናት ከቀረቡት ሐተታዎች መካከል ‹‹አዋሽ›› በተሰኘው ሥነ ግጥማቸው ዙርያ የሰጡትን አንድምታ እንዲህ አቅርበነዋል፡፡

*********
ጸጋዬ ገብረ መድኅን በመጨረሻው ዘመኑ የራሱን ሥነ ግጥሞች ባነበበት ሲዲ ላይ ስለ አዋሽ ሥነ ግጥም ምሳሌያዊነት ሲናገር በሌሎችም አገሮች የየአገሩ ባለቅኔዎች ታላላቅ ወንዞቻቸውን በአገራዊ ምሳሌአዊነት እንደሚወክሏቸው ያነሣል፡፡ ታላቁ ቴብስ በእንግሊዝ፣ ሚሲሲፒ በአሜሪካ፣ ቮልጋ ወይም ዶን በሩሲያ፣ በአገራዊ ምሳሌያዊነታቸው የየአገሩን ታሪክና ባህል ሲወክሉ መኖራቸውን ይናገራል፡፡

በ‹‹ምሥጢረኛው ባለቅኔ›› መጽሐፌ የአዋሽን ምሳሌያዊነት በሁለት መልክ ለማሳየት ሞክሬ ነበር፡፡ አንደኛው ባለቅኔው ራሱ እንዳለው ባገራዊ ምሳሌያዊነቱ ነው፡፡ ሁለተኛውና ባለቅኔው ያላለው ደግሞ አዋሽ የባለቅኔው የገዛ ሕይወቱ ምሳሌያዊ ውክልና መሆኑን ነው፡፡ አገራዊ ምሳሌያዊነቱን በሁለተኛ ደረጃ ለማስረዳት እስቲ በመጀመርያ አዋሽ የጸጋዬን ሕይወት በምን መልክ እንደወከለ ለማሳየት ልሞክር፡፡

በእኔ ንባብ አዋሽ ሥነ ግጥም ላዩን ወይም ሰሙን ብቻ ላነበበ ስለወንዙ የተጻፈ መወድስ ሊመስለው ይችላል፡፡ ሥነ ግጥሙ ባለሦስት ንጣፍ የቅኔ አነባበሮ መሆኑን እምንረዳው ወርቅና ምናልባትም አልማዙ ሲገለጡልን ነው፡፡ ከእዚህ ላይ ወርቁ ወይም ሁለተኛው ንጣፍ የግጥሙ አገራዊ ውክልና ነው፡፡

በዚህ ሥነ ግጥም አዋሽ በአገራችን ባህልና የታሪክ ጉዞ ተመስሏል፡፡ በለጋስነቱ በባለጸግነቱ ያገርን ዙርያ ጥምጥም ሁሉ በማዳረሱ ስልም በንፉግነቱ በአገራችን የታሪክ ጉዞ ተመስሏል፡፡ ዘለዓለም በማያቋርጥ ጉዞው በስተመጨረሻው አረህ አለምልሞ በረሃ ላንቃ በመዋጡ ፍሬ ሊያፈራ ባለመቻሉ በታላቅ ሐዘን ባገራችን የታሪክ ጉዞ ተመስሏል፡፡ በሌላም በኩል በተስፈኝነቱ ወደ ምሥራቅ በመፍሰሱ በታሪክ በረሃ ውስጥ ከዘለዓለም እስከዘለዓለም ሲፈስ ጨርሶ በማይሞተውና በማይደመሰሰው በተስፈኛ መንፈሳችን ተመስሏል፡፡

‹‹እስከ መቼ ይሆን አዋሽ ......... አዋሽ በቃኝ አትል ቆራጥ፣
ማን ያስተማረህ ፈሊጥ ነው አረህ ለማለምለም መዋጥ፣
አሻቅበህ ወደ ምሥራቅ ወደ ጀምበር መውጫ መናጥ፣
ሰምጠህ ልትቀር በሐሩር ማጥ፣››
የሐበሻ ታሪክ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የተዘረጋው የሐበሻ ታሪክና ባህል በተለይም ደግሞ ጸጋዬ ባለፈበት ዘመን በዚያ ሁሉ የዘመን ጉዞ በመጨረሻ ሽሚያና ቅሚያ የነገሠበት እንደጸጋዬ አገላለጽ ፍግ የሚለመልምበት ፍቅር የሞተበትን ትውልድ በማፍራት/ በማለምለሙ ሲያዝን አዋሽን በአገራችን ጉዞ ተወክሎ እናየዋለን፡፡

ይሁን እንጂ ይህ ምሳሌ የጸጋዬ ሥነ ጥበባዊ ሕይወት ምሳሌም ጭምር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሦስተኛው ንጣፍ መሆኑ ነው፡፡

ሁሉም እንደሚያውቀው ጸጋዬ ትውልድ ቀዬው ከመጫ ጊንጪ በስተደቡብ ሲል ቦዳ አቦ ነው፡፡ የአዋሽ ወንዝም መነሻ ከዚያው ከጊንጪ አላባ ጣፋ ተራራ ግርጌ ነው፡፡ የጸጋዬ የሥነ ጥበብ መንፈስና ሕይወት አገር ምድሩን ሁሉ ዙሮ በመጨረሻ በንፉግ ባህል በረሃ ተውጦ እንዲቀር አዋሽም አገር ምድሩን አካልሎ ከአሳይታ ማዶ አፋምቦ ተራራ ግርጌ አሸዋ ውስጥ ሰምጦ ይቀራል፡፡

‹‹መጫ ቋጥሮ ሸዋ ጸንሶ ሰባት ቤት ጉራጌ አርግዞ፣
ከዳዳ ምንጭ አሩሲ እምብርት ከነቅሪቱ ተጉዞ፣
ከአላባ ጣፋ ሼህ ሁሴን አዳል ሞቲ ሽሉን ይዞ፣
ከከረዩ ማታ ሓራ ከኢቱ እስከ አፋር አምጦ፣
አሸዋ ነክሶ ቀረ አዋሽ ከነጽንሱ አረህ ሰምጦ፣
በምድረ በዳ ጉረሮ በረሃ ላንቃ ተውጦ፤›› ይለናል፡፡ በዚህ የአዋሽ የአገር ዙር ጥምጥም ጉዞና ፍጻሜ ውስጥ ጸጋዬ የራሱን ምስል ሥሎልናል፡፡ እርሱ በሥነ ጥበቡ ዘልቆ ያልገባበት የአገርና የባህል እልፍኝ የለም፡፡ በእሳት ወይ አበባ ሥነ ግጥም መድበል እንኳ ከዓባይ ኑቢያ ዘመን ሥልጣኔ አንሥቶ የኦሮሞን ጋዳ ሥርዓት፣ ባህልና ለዛ በ‹‹አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ››፣ የኦሮሞን ጀግና መንፈስ ‹‹በቦረን የሃዩ አላኬ ሊበን ቀረርቶ››፣ በ‹‹አንኮበር›› የአመሃየስ በር የቤተ አምሃራን ፖለቲካና ባህል፣ ወደ ውስጥ ዘልቆ፣ የሩቁን አቅርቦ ከታሪክና ከባህላችን ሊያስተዋውቀን ሲቃትት እናደምጠዋለን፡፡ ከታሪክ ምዕራፎቻችን ዓድዋና ማይጨው፣ መተማና ዶጋሊን፣ በምናቡ አቅርቦ በዘለለት ሩጫ ዝንጋኤ ማንነቱ ለጠፋበት ትውልድ የማን ልጅነቱን ሊያስታውስ ሲጥር እንሰማዋለን፡፡ ከዘመን ጀግኖቻችንን ረስተን ማንነታችን እንዳይሰወርብን ቴዎድሮስን፣ ጴጥሮስን፣ ዮሐንስን፣ ከሞት አስነሥቶ ሁለተኛ ልደት ሲሰጣቸው በመድረክም በሥነ ግጥምም ስንመለከት ኖረናል፡፡ በጥሞና ዘልቀን ካስተዋልናቸው እኒህና ሌሎቹ ሁሉ ጥልቀታቸውና ለኛ ትውልድ ሕይወት ያላቸው ፋይዳ ታላቅ ነው፡፡ እናም ጸጋዬ ይህን በመሰለው የሥነ ጥበብ ሕይወቱ ነው አገር ምድርን በሚያካልለው በአዋሽ የተመሰለው፡፡ ጸጋዬ የሥነ ጥበባዊ ሥነ ልቡናውን የጸነሰው ከትውልድ መንደሩ ከአምቦ ነው፡፡ ከመጫ፡፡ አፈጻጸሙም ‹‹በንፉግ ባህል ውስብስብ ጫካ በቁም እያለ መረሳት፣ አሊያም ቢታወስም ለቁም ነገሩ ዋጋ የማይሰጥ ውዳሴ ከንቱ መሞካሸት በቀር፣ የዘራውን ሳይቅም የወለደውን ሳይስም በከንቱ የመቅረቱ ምሳሌ ነው፡፡››

‹‹መጫ ቋጥሮ ሸዋ ጸንሶ ሰባት ቤት ጉራጌ አርግዞ
ከዳዳ ምንጭ አሩሲ እምብርት ከነቅሪቱ ተጉዞ
ከአላባ ጣፋ ሼህ ሁሴን አዳል ሞቲ ሽሉን ይዞ
ከከረዩ ማታ ሓራ ከኢቱ እስከ አፋር አምጦ
አሸዋ ነክሶ ቀረ አዋሽ ከነጽንሱ አረህ ሰምጦ፡፡››
ይህም የተሣለልን በዕድሜ ልክ ጉዞ በአዋሽ ጉዞ ተመስሎ ነው፡፡ ወደ አፋር በረሃ ዘልቆ የአዋሽን ጉዞ ላስተዋለ ያን ሁሉ ዘመን ሲያለመልም የኖረውን አረህና አሜኬላ በሐዘን ይታዘባል፡፡ የጸጋዬም ረዥም የሥነ ጥበብ ሕይወት በታሪክ ብያኔ ሰበብ እምነትና ፍቅሩ የነጠፈ፣ ይልቁንም ለመጪው ትውልድ እሚያወርሰው ‹‹የሰብእና ብርሃን›› የሌለው ትውልድ ሲፈጠር በማስተዋሉ በምስጢር ከራሱ የተዋቀሰበት ሥነ ግጥም መሆኑን እናስተውላለን፡፡

‹‹እስከ መቼ ይሆን አዋሽ ..... አዋሽ በቃኝ አትል ቆራጥ
ማን ያስተማረህ ፈሊጥ ነው አረህ ለማለምለም መዋጥ
አሻቅበህ ወደ ምሥራቅ ወደ ጀምበር መውጫ መናጥ
ሰምጠህ ልትቀር በሐሩር ማጥ፡፡››
ይህን አረህ የማለምለም ርግማን በአዋሽ ብቻ ሳይሆን በቴዎድሮስ ምሳሌ በሣለው የራስ ምስልም ውስጥ እናገኘዋለን፡፡
‹‹ታዲያ እንግዲህ አንቺ ኢትዮጵያ እኛስ ልጆችሽ ምንድነን
አመንኩሽ ማለት እማንችል ፍቅራችን እሚያስነውረን
ዕዳችን የሚያስፎክረን
ቅንነት የሚያሳፍረን ቂማችን የሚያስደስተን
ኧረ ምንድነን? ምንድነን?››
አሜኬላ እሚያብብን
ፍግ እሚለመልምብን
ከአረም ጋር ያፈራን ጊንጦች ከእንክርዳድ ያልተለየን ዘር
ግርዱ ከምርቱ ተማጥቆ ከቶ ያልተበራየን መከር....››
በአዋሽ ሥነ ግጥም የተሣለው የጸጋዬ ውስጣዊ የኪሳራ ስሜትና ትካዜ ተስፋ ላለመቁረጥ የተደረገ ውሳጣዊ ሙግት ነው፡፡ ይሁንና ይኸው ውሳጣዊ ትግል ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት የታሪካችን ጉዞ ምስልም ነው፡፡

                                                   እሳት ወይ አበባ


እሳት ወይ አበባ

 ሌት ከዋክብቱ  እንደ ፀደይ
አጥለቅልቆን  በቀይ አደይ
ሰማዩ  ሥጋጃ  አጥልቆ
ተሽለምልሞ  አንጸባርቆ
ፈክቶ አሸብርቆ  ደምቆ
በአዝመራ  በአጥቢያ  ዐፀድ  ሰፍኖ
የዓደይ  አዝርዕት  ተከሽኖ
በዕንቁጣጣሽ  ሰብል  ታጥኖ
ኢዮሃ  አበባዬ  ሆኖ፥
ጨረቃዋ  ከቆባዋ፥  ከሽልምልሚት  እምቡጧ
ብላ ከሰንኮፈንዋ፥ ተንዠርግጎ የእንኮይ ቡጧ፥
ድንግል  ጽጌ-ረዳ  ፈልቃ
ፍልቅልቂት  ድምቡል ቦቃ
ተንሠራፍታ  የአበባ  ጮርቃ፥
ታድያን  ብሌኑ  የጠጠረ
ባሕረ-ሃሳቡ የከረረ
የውበት ዓይኑ የታወረ
ልበ-ሕሊናው  የሰለለ
አይ፥ አበባ አይደለም አለ፤
አይ፥ እሳት አይደለም አለ፤
ያልታደለ።
ሰማይ  ጨለማ  ነው እንጂ፥  እሳት አደል ብሎ ካደ
እቶን  ባይኑ  እየነደደ።
ከዋክብቱ  እንደ  ችቦ
በነበልባል  ወርቀ  ዘቦ
ከፅንፍ  ፅንፍ  አውለብልቦ
ደመራው  እየተመመ
እየፋመ  እየጋመ
ደመና  እንደንዳድ  ሲነድ
መንጸባርቅ  ሰደድ  ሲወርድ፥
በራሪ  ኮከብ  ተኩሶ
በአድማሳት  እሳት  ለኩሶ
ይኸ እንደኔና  እንዳንቺው፥  የውበት ዓይኑ  የሰለለ
ሰማይ ጨለማ ነው እንጂ፥  እሳት እኮ አይደለም አለ፥
ያልታደለ።

ይቅር ብቻ  አንናገርም፥
እኔና  አንቺ  አንወያይም፤
ለውይይት  አልታደልንም
እንዲያው ዝም፥ እንዲያው ዝምዝም።
አበባ አንሆን ወይ እሳት
ተጠምደን  በምኞት  ቅጣት
ሰመመን  ባጫረው  መዓት
ዕድሜ አችንን እንዳማጥናት፤

እሳት አንሆን ወይ አበባ
በሕቅ  እንቅ  ስንባባ
ባከነች  ልጅነታችን፥ እየቃተትን ስናነባ
ሳንፈጠር  በሞትንባት
ሳናብብ  በረገፍንባት
ሳንጠና ባረጀንባት
አበባ ወይንም እሳት፥  መሆኑን ብቻ አጣንባት።

Friday, May 4, 2012

በውቀቱ ስዩም

www.facebook.com/tarikuasefaክልክል ነው

ማጨስ ክልክል ነው
ማፍዋጨት ክልክል ነው
መሽናት ክልክል ነው
ግድግዳው በሙሉ ተሰርቶ በክልክል
የቱ ነው ትክክል?
ትንሽ ግድግዳና ትንሽ ኃይል ባደለኝ
"መከልከል ክልክል ነው"፤ የሚል ትዕዛዝ አለኝ፡፡


(በእውቀቱ ስዩም፣ የ፣ሣት ዳር ሐሳቦች፣ 2000)
 ደመወዙን ቢጥል
አንስተው ጠጡበት
ባርኔጣውን ቢጥል
ወስደው ደመቁበት
ከዘራውን ቢጥል
ተመረኮዙበት
በሄደበት ሁሉ
እየተከተሉ
በጣለው ሲያጌጡ
በጣለው ሲያተርፉ
ራሱን ሲጥል ግን
አይተውት አለፉ

በውቀቱ ስዩም
(ካንድምታ ላይ የተወሰደ )
 መሆን አለመሆን

በመሆን እና ባለመሆን
በማድረግ እና ባለማድረግ
በሁለት ታዛዦች ስር መውደቅ ነው
ሰው የመሆን ትልቅ ህግ
ሊኖሩት በማይፈቅዱት ህግ
ሊፈጽሙት በማይሹት ስህተት
በጣምራ ግጭቶች መሃል መቆም ነው ሰው የመሆን ሰውነት
ይሄ ሁሉ ፍጡር ይሄ ሁሉ ፍጡር
በፍጥረት መድረክ ላይ የሚርመሰመሰው
ላንዲት ቅጽበት እንካን ሰው ሆኖ አያውቅም ሰው ሊሆን ጽንስ ነው
ሰው እስኪሆን ድረስ አንዳንድዜ አምላክ አንዳንዴ ሰይጣን ነው።
ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን
መሸ ደግሞ አምባ ልውጣ!

አምባ ወጥቼ እኩለ-ሌት ፤ ስለት ገብቼ በስሟ
ከርሞ ሰይጣን በሷ አስቶኝ፤ ልገላገል ከህመሟ
ጠበሏ አፋፍ በጨረቃ፤ ደጋግሜ፤ ማህሌት ቆሜ
ሆዴ ቃትቶ ባር ባር ብሎ፤እርቃኔን ከሷ ታድሜ
ደጀ ሰላሟን በአራት እግር፤ ተንበርክኬ ተሳልሜ
በስጋዬ እሚነደውን፤ በጸሎት ላቤ አጣጥሜ
እፎይ ብዬ አመስግኜ፤ ውዳሴዋን ደጋግሜ...
ገና ከደጅዋ እልፍ ሳልል፤ ደሞ ይምጣ የቁም ህልሜ?
ሌት በጥምቀቷ የነጣው፤ ነጋ፤ ደፈረሰ ደሜ።
ለሷ እንጂ ለኔ አልያዘልኝ፤ አዬ የስለት አታምጣ!
በውጣ ውረድ በጠበል፤ ባሣር ወዜ ቢገረጣ
ልክፍቷ እንደሁ አልለቀቀኝ፤ መሸ ደሞ አምባ ልውጣ!

ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድሀን፣ እሳት ወይ አበባ

Thursday, May 3, 2012

ይድረስ ለእናት አለም


ይድረስ ለእናት አለም፡-www.facebook.com/tarikuasefa

በጣም ለምወድሽ እናቴ እናት አለም ! እንደምን ሰንብተሻል

አባበዬስ እንዴት ነው? እኛ ከወንድም ጋሼ ፀባይ መለዋወጥ

በስተቀር ደህና ነን፡፡ እናት ዓለም ብቻ አንድ ወንድ ልጅሽን ያቺ

ቀልቃላ ገርል ፍሬንዱ ምን እንዳስነካችው ባይታወቅም አብሮን

እንዳልተወለደ አሁንማ ስልኩንም ለማንሳት ኮርቷል፡፡

በየሳምንቱ እሷን ይዞ በየሀገሩ መብረር አምጥቷል፡፡

እናት አለም! እናንተ ለፍታችሁ አንዴ ፈረንሳይ ት/ቤት፤

አንዴ ፈረንጅ ሀገር ብር እየመነዘራቸሁ አስተምራቸሁ ዛሬ

ይቺ ከይሲ በአናት መጥታ የተዘጋጀ እና ያማረ ቤት ልትገባ

ዳር ዳር ትላለች፡፡ በዛ ላይ ደግሞ እሱ እሷን ተዋወኩ ብሎ

አዲሰ ማርቼድስ አውጥቶ የድሮውን ቢ..ኤም..ደብሊው ለእኔ

ይሰጠኛል ስል እሷው በቀደም ይዛው ስትደናብር መሀል ከተማ

Aየኋት፡፡ በዛ ላይ አለባበሷን ብታይ እኮ ጭንቅላትሽን ይዘሽ

ትጮሂያለሽ፡፡ የተወለደ ሀጻን ጭንቅላት የሚያካክሉትን

ጡቶቿን እያሳየች ነው የምትሄደው፡፡ ትንሽ እንኳን እፍረት

የሌላት ጉድ በየድግሱ ቤት ወንበር እያለ እሱ ላይ ነው

የምትቀመጠው፡፡ ሌላው ደግሞ እንደ በሽተኛ እሱ ነው

የሚያጎርሳት ብትሞት በእጇ አትበላም፡፡ እኔማ ገና ሳያት ነው

ደሜ የሚፈላው፡፡

ብቻ ልጅሽን ምን እንዳስነካችው እራስሽ መጥተሽ

ብትጠይቂው ይሻላል፡፡ በዚያን ሰሞን ቹቹ የመኪናዋ ቁልፍ

ጠፍቶ ስራ ውሰዳት ብዬ ብደውልለት ታከሲ ይዛ ትሂድ ስብሰባ

አለበኝ አለኝ፡፡ ለድሮው የእኛ ነገር የማይሆንለት ይኸው እሷን

ካገኘ ወንድምነቱን ሁሉ ረስቶታል፡፡ ከሁሉ ከሁሉ የምፈራው

አውቃ አርግዛበት ጠቅልላ ለመግባት ሠርጌን ደግስ እንዳትለው

ነው፡፡

እንደው አናት አለም እሷን ካገኘ ፀባዩ ሁሉ ተቀያይሯል፡፡

ባለፈውማ ይባስ ብሎ ለልደቱ የገዛሁለትን የሱን ቱታ ለብሳ

ስፖርት ስትሰራ ስፖርት ቤት አገኘኋት፡፡ ደግሞ አማረብኝ ብላ

ያንን እሱው ያሰራላትን ነጭ ጥርሶቿን ታሳየኛለች፡፡

እንደማትወደኝ እኮ ያስታውቅባታል!! ከሁሉ ከሁሉ ቹቹ ታክሲ

ይዛ ትሂድ ያለውን አልረሳውም፡፡ እናት አለም መቼም ጉድሽን

የሚነገርሽ የለም ብዬ ነው የምጽፍልሽና ነገ ጠዋት አንቺንም

በዚች በቀዥቃዣ ሳይለውጥሽ አንድ ነገር አድርጊ፤ ምንም

ቢሆን እኛ ሥጋዎቹ ነን፤ ከአንድ ሆድ የወጣነውና አንድ ጡት

ጥበተን ያደግነው እኛ ነን፡፡ እሷ ባዳ ናትና አንድ ነገር አድርጊ፡፡



                                                      ልጅሽ ሳሮን

የእናት አለም የመልስ ደብዳቤ

ለምወድሽ ልጄ ሳሮንዬ ለመሆኑ የላከሺልኝን ደብዳቤ ሰትጽፊልኝ ምን

ዓይነቱ ስይጣን ነው ሰፍሮበሽ የነበረው! እንዲህ ዓይነት ልጅ ነው

የወለድኩት አሰኘኝ፡፡ እግዚአብሔር የቀንና የማታ ጸሎቴን ሰምቶ ለአንድ

ወንድ ልጄ ውሃ አጣጭ የትዳር ጓደኛ ቢሰጠው የአንቺ እንቅልፍ ማጣት

ምን ይባላል?

የእኔ ልጅ! እንዳልሽው ከአንድ ሆድ የወጣችሁ አንድ ጡት ጠብታችሁ

ያደጋችሁ ወንድምሽ ነው፡፡ ወንድም እህቱን እንዲያገባ ሃይማኖታችንም

ባህላችንም አይፈቅድም፡፡ ወንድምሽን አንቺ አታገቢው፤ ምን አድርጊ ነው

የምትያት? የእኔ ልጅ ይኼው እሷን ካገኘ ጊዜ ጀምሮ የላከልኝ ፎቶ

ይኸው መልኩም መለስ ብሏል፡፡ በሳምንት በሳምንትም ይደውልልኛል፡፡

እሷንም በስልክ ደውሎ አስተዋውቀኝ፡፡ አደራ ብያትም ይኼው የሆቴል

ምግብ ከበላ ሰንበቷል፡፡ የልጄን ደስታ በድምፁ አውቀዋለሁ፡፡ ይኼው

እናንተ ስትለመኑ ሰው እየፈለግን ነው ያላችሁትን መድኀኒት እንኳን

እሷም አይደለች እንዴ የፊት ቅባት ሳይቀር ጨምራ በፖስታ ቤት

የላከችልኝ፡፡ ሌላው ደግሞ ነርስ ነች አለኝ፡፡ ልጄ ቢያመው እንኳን አጠገቡ

አለችለት፡፡

አንዳታረግዝ ነው የምፈራው አልሺኝ? በየቤተክርስቲያኑ የምሳለው ስለቴ

ደርሶልኝ የሱን ፍሬ ሳልሞት ባይ ምናለበት፡፡ አንድ ሳይሆን መንታ መንታውን

ባረገዘችልኝ፡፡ አንቺ የሰው ኑሮ ውስጥ ገብተሸ ከምትበጠብጪ ሰው መናቁን

ትተሸ ብታገቢ ለወሬም ጊዜ አየኖርሽም ነበር፡፡

የእኔ ልጅ! ጡቷን ማሳየት ቀርቶ ራቁቷን ብተሄድ ፖሊስ ካልያዛትና ልጄ

ከወደዳት አንቺ ምን ጥልቅ አደረገሽ? ቢወዳትም አይደል እንዴ እዚህ ድረስ

ደውሎ ያስተዋወቀኝ፡፡ የኔ ልጅ መፅሀፉም የሰው ልጅ እናት እባቱን ይተዋል፤

ከሚሰቱ ወይ ከባሉ ጋር እንድ ይሆናል ነው እንጂ የሚለው ወንድም እህቱን

ያገባል አይልምና ወደ መንፈስሽ ተመልሰሽ አምላክሽን ይቅርታ ጠይቂ፡፡

የወንድምነቱን ከሚገባው በላይ አድርጓል ወይስ እድሜ ዘላለሙን እናንተን

ሲያስተምርና መኪና ሲገዛ እንዲኖር ነው ምኞትሽ፡፡

ልጄ! ልብ ብለሽ አያትሽ የነገረኝን ይሄንን አፈ ታሪክ አንበቢ፡፡

“ሚስት ከባልዋ ተጣልታ ዛሬውኑ መጥታችሁ ካላፋታቸሁኝ ራሴን

እገላለሁ ብላ አናት አባቷ ጋ መልእከተኛ ትልካለች፡፡ እናትና አባትም

ደንግጠው ሊያፋቱ ሲከንፉ በሌሊት ልጃቸው ቤት ይሄዳሉ፡፡ ድንገት በሩን

ከፍተው ሲገቡ ልጃቸው ከአልጋዋ ዘላ ወርዳ ራቁቷን ትቆማለች፡፡

ድንገትም በር የከፈቱት እናትና አባቷ መሆኑን ስታይ አፍራ ቶሎ ብላ

ፊቷን ወደ ባሏ ጀርባዋን ደግሞ ወደ እናትና አባቷ አዞረች፡፡ ምንም

እንኳን ልትፈታው የተዘጋጀችው ባሏ ቢሆንም ባሏን ሳታፍር እናትና

አባቷን አፈረች፡፡”

ልጄ ሳሮን የእናትና የአባት ፍቅር ዘላለማዊ ቢሆንም የወላጅንም ውለታ

መመለስ ተገቢ ቢሆንም ከባልና ከሚስት የቀረበ የለም፡፡ ስለዚህም ነው

ባልና ሚስት አንድ አካል አንድ አምሳል ናቸው የሚባለውና ቦታሽን

Aውቀሽ የሰውን ሕይወት አትበጥብጪ፡፡ አፍ አለኝ ብለሽም እንዲህ

አይነት አሉባልታ ሁለተኛ እንዳትጽፊልኝ፡፡ አንቺ አግብተሸ ብትወልጂ

ወንድምሽ ደስ እንደሚለው ሁሉ ለእሱም አንቺ ደስ የበልሽ፡፡

እግዚአብሔር ጥሩ ልቦና እንዲሰጥሽ እጸልይልሻለሁ፡፡

እናትሽ እናት እለም