ባለቅኔውና ጸሐፌ ተውኔቱ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን (1928-1998)
በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ሁነኛ ስፍራ አላቸው፡፡ በአማርኛና በእንግሊዝኛ በጻፏቸው ልጨኛ (ማስተርፒስ)
ሥራዎቻቸውም ግኑን ናቸው፡፡
ከአምስት ዓመት በፊት የካቲት 18 ቀን 1998 ዓ.ም. ያረፉት ሎሬት ጸጋዬ ከጻፏቸው መጻሕፍት አንዱ ‹‹እሳት ወይ አበባ›› የሥነ ግጥም መድበል ነው፡፡
‹‹ምሥጢረኛው
ባለ ቅኔ›› የተሰኘ በደራሲው ጥበባዊ ሕይወት ዙሪያ መጽሐፍ ያሳተሙት አቶ ሚካኤል ሺፈራው፣ በቅርቡ ‹‹አንድምታ
ወሐተታ ዘጸጋዬ ገብረ መድኅን›› በሚል ርእስ በአንድ መድረክ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበው ነበር፡፡
በ‹‹እሳት ወይ አበባ›› መድበል ላይ ባተኮረው ጥናት ከቀረቡት ሐተታዎች መካከል ‹‹አዋሽ›› በተሰኘው ሥነ ግጥማቸው ዙርያ የሰጡትን አንድምታ እንዲህ አቅርበነዋል፡፡
*********
ጸጋዬ
ገብረ መድኅን በመጨረሻው ዘመኑ የራሱን ሥነ ግጥሞች ባነበበት ሲዲ ላይ ስለ አዋሽ ሥነ ግጥም ምሳሌያዊነት ሲናገር
በሌሎችም አገሮች የየአገሩ ባለቅኔዎች ታላላቅ ወንዞቻቸውን በአገራዊ ምሳሌአዊነት እንደሚወክሏቸው ያነሣል፡፡ ታላቁ
ቴብስ በእንግሊዝ፣ ሚሲሲፒ በአሜሪካ፣ ቮልጋ ወይም ዶን በሩሲያ፣ በአገራዊ ምሳሌያዊነታቸው የየአገሩን ታሪክና
ባህል ሲወክሉ መኖራቸውን ይናገራል፡፡
በ‹‹ምሥጢረኛው ባለቅኔ›› መጽሐፌ የአዋሽን ምሳሌያዊነት በሁለት
መልክ ለማሳየት ሞክሬ ነበር፡፡ አንደኛው ባለቅኔው ራሱ እንዳለው ባገራዊ ምሳሌያዊነቱ ነው፡፡ ሁለተኛውና ባለቅኔው
ያላለው ደግሞ አዋሽ የባለቅኔው የገዛ ሕይወቱ ምሳሌያዊ ውክልና መሆኑን ነው፡፡ አገራዊ ምሳሌያዊነቱን በሁለተኛ
ደረጃ ለማስረዳት እስቲ በመጀመርያ አዋሽ የጸጋዬን ሕይወት በምን መልክ እንደወከለ ለማሳየት ልሞክር፡፡
በእኔ
ንባብ አዋሽ ሥነ ግጥም ላዩን ወይም ሰሙን ብቻ ላነበበ ስለወንዙ የተጻፈ መወድስ ሊመስለው ይችላል፡፡ ሥነ ግጥሙ
ባለሦስት ንጣፍ የቅኔ አነባበሮ መሆኑን እምንረዳው ወርቅና ምናልባትም አልማዙ ሲገለጡልን ነው፡፡ ከእዚህ ላይ ወርቁ
ወይም ሁለተኛው ንጣፍ የግጥሙ አገራዊ ውክልና ነው፡፡
በዚህ ሥነ ግጥም አዋሽ በአገራችን ባህልና
የታሪክ ጉዞ ተመስሏል፡፡ በለጋስነቱ በባለጸግነቱ ያገርን ዙርያ ጥምጥም ሁሉ በማዳረሱ ስልም በንፉግነቱ በአገራችን
የታሪክ ጉዞ ተመስሏል፡፡ ዘለዓለም በማያቋርጥ ጉዞው በስተመጨረሻው አረህ አለምልሞ በረሃ ላንቃ በመዋጡ ፍሬ ሊያፈራ
ባለመቻሉ በታላቅ ሐዘን ባገራችን የታሪክ ጉዞ ተመስሏል፡፡ በሌላም በኩል በተስፈኝነቱ ወደ ምሥራቅ በመፍሰሱ
በታሪክ በረሃ ውስጥ ከዘለዓለም እስከዘለዓለም ሲፈስ ጨርሶ በማይሞተውና በማይደመሰሰው በተስፈኛ መንፈሳችን
ተመስሏል፡፡
‹‹እስከ መቼ ይሆን አዋሽ ......... አዋሽ በቃኝ አትል ቆራጥ፣
ማን ያስተማረህ ፈሊጥ ነው አረህ ለማለምለም መዋጥ፣
አሻቅበህ ወደ ምሥራቅ ወደ ጀምበር መውጫ መናጥ፣
ሰምጠህ ልትቀር በሐሩር ማጥ፣››
የሐበሻ
ታሪክ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የተዘረጋው የሐበሻ ታሪክና ባህል በተለይም ደግሞ ጸጋዬ ባለፈበት ዘመን በዚያ
ሁሉ የዘመን ጉዞ በመጨረሻ ሽሚያና ቅሚያ የነገሠበት እንደጸጋዬ አገላለጽ ፍግ የሚለመልምበት ፍቅር የሞተበትን
ትውልድ በማፍራት/ በማለምለሙ ሲያዝን አዋሽን በአገራችን ጉዞ ተወክሎ እናየዋለን፡፡
ይሁን እንጂ ይህ ምሳሌ የጸጋዬ ሥነ ጥበባዊ ሕይወት ምሳሌም ጭምር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሦስተኛው ንጣፍ መሆኑ ነው፡፡
ሁሉም
እንደሚያውቀው ጸጋዬ ትውልድ ቀዬው ከመጫ ጊንጪ በስተደቡብ ሲል ቦዳ አቦ ነው፡፡ የአዋሽ ወንዝም መነሻ ከዚያው
ከጊንጪ አላባ ጣፋ ተራራ ግርጌ ነው፡፡ የጸጋዬ የሥነ ጥበብ መንፈስና ሕይወት አገር ምድሩን ሁሉ ዙሮ በመጨረሻ
በንፉግ ባህል በረሃ ተውጦ እንዲቀር አዋሽም አገር ምድሩን አካልሎ ከአሳይታ ማዶ አፋምቦ ተራራ ግርጌ አሸዋ ውስጥ
ሰምጦ ይቀራል፡፡
‹‹መጫ ቋጥሮ ሸዋ ጸንሶ ሰባት ቤት ጉራጌ አርግዞ፣
ከዳዳ ምንጭ አሩሲ እምብርት ከነቅሪቱ ተጉዞ፣
ከአላባ ጣፋ ሼህ ሁሴን አዳል ሞቲ ሽሉን ይዞ፣
ከከረዩ ማታ ሓራ ከኢቱ እስከ አፋር አምጦ፣
አሸዋ ነክሶ ቀረ አዋሽ ከነጽንሱ አረህ ሰምጦ፣
በምድረ
በዳ ጉረሮ በረሃ ላንቃ ተውጦ፤›› ይለናል፡፡ በዚህ የአዋሽ የአገር ዙር ጥምጥም ጉዞና ፍጻሜ ውስጥ ጸጋዬ የራሱን
ምስል ሥሎልናል፡፡ እርሱ በሥነ ጥበቡ ዘልቆ ያልገባበት የአገርና የባህል እልፍኝ የለም፡፡ በእሳት ወይ አበባ ሥነ
ግጥም መድበል እንኳ ከዓባይ ኑቢያ ዘመን ሥልጣኔ አንሥቶ የኦሮሞን ጋዳ ሥርዓት፣ ባህልና ለዛ በ‹‹አቴቴ ዱብራ
ኦሮሞ››፣ የኦሮሞን ጀግና መንፈስ ‹‹በቦረን የሃዩ አላኬ ሊበን ቀረርቶ››፣ በ‹‹አንኮበር›› የአመሃየስ በር
የቤተ አምሃራን ፖለቲካና ባህል፣ ወደ ውስጥ ዘልቆ፣ የሩቁን አቅርቦ ከታሪክና ከባህላችን ሊያስተዋውቀን ሲቃትት
እናደምጠዋለን፡፡ ከታሪክ ምዕራፎቻችን ዓድዋና ማይጨው፣ መተማና ዶጋሊን፣ በምናቡ አቅርቦ በዘለለት ሩጫ ዝንጋኤ
ማንነቱ ለጠፋበት ትውልድ የማን ልጅነቱን ሊያስታውስ ሲጥር እንሰማዋለን፡፡ ከዘመን ጀግኖቻችንን ረስተን ማንነታችን
እንዳይሰወርብን ቴዎድሮስን፣ ጴጥሮስን፣ ዮሐንስን፣ ከሞት አስነሥቶ ሁለተኛ ልደት ሲሰጣቸው በመድረክም በሥነ ግጥምም
ስንመለከት ኖረናል፡፡ በጥሞና ዘልቀን ካስተዋልናቸው እኒህና ሌሎቹ ሁሉ ጥልቀታቸውና ለኛ ትውልድ ሕይወት ያላቸው
ፋይዳ ታላቅ ነው፡፡ እናም ጸጋዬ ይህን በመሰለው የሥነ ጥበብ ሕይወቱ ነው አገር ምድርን በሚያካልለው በአዋሽ
የተመሰለው፡፡ ጸጋዬ የሥነ ጥበባዊ ሥነ ልቡናውን የጸነሰው ከትውልድ መንደሩ ከአምቦ ነው፡፡ ከመጫ፡፡ አፈጻጸሙም
‹‹በንፉግ ባህል ውስብስብ ጫካ በቁም እያለ መረሳት፣ አሊያም ቢታወስም ለቁም ነገሩ ዋጋ የማይሰጥ ውዳሴ ከንቱ
መሞካሸት በቀር፣ የዘራውን ሳይቅም የወለደውን ሳይስም በከንቱ የመቅረቱ ምሳሌ ነው፡፡››
‹‹መጫ ቋጥሮ ሸዋ ጸንሶ ሰባት ቤት ጉራጌ አርግዞ
ከዳዳ ምንጭ አሩሲ እምብርት ከነቅሪቱ ተጉዞ
ከአላባ ጣፋ ሼህ ሁሴን አዳል ሞቲ ሽሉን ይዞ
ከከረዩ ማታ ሓራ ከኢቱ እስከ አፋር አምጦ
አሸዋ ነክሶ ቀረ አዋሽ ከነጽንሱ አረህ ሰምጦ፡፡››
ይህም
የተሣለልን በዕድሜ ልክ ጉዞ በአዋሽ ጉዞ ተመስሎ ነው፡፡ ወደ አፋር በረሃ ዘልቆ የአዋሽን ጉዞ ላስተዋለ ያን ሁሉ
ዘመን ሲያለመልም የኖረውን አረህና አሜኬላ በሐዘን ይታዘባል፡፡ የጸጋዬም ረዥም የሥነ ጥበብ ሕይወት በታሪክ ብያኔ
ሰበብ እምነትና ፍቅሩ የነጠፈ፣ ይልቁንም ለመጪው ትውልድ እሚያወርሰው ‹‹የሰብእና ብርሃን›› የሌለው ትውልድ
ሲፈጠር በማስተዋሉ በምስጢር ከራሱ የተዋቀሰበት ሥነ ግጥም መሆኑን እናስተውላለን፡፡
‹‹እስከ መቼ ይሆን አዋሽ ..... አዋሽ በቃኝ አትል ቆራጥ
ማን ያስተማረህ ፈሊጥ ነው አረህ ለማለምለም መዋጥ
አሻቅበህ ወደ ምሥራቅ ወደ ጀምበር መውጫ መናጥ
ሰምጠህ ልትቀር በሐሩር ማጥ፡፡››
ይህን አረህ የማለምለም ርግማን በአዋሽ ብቻ ሳይሆን በቴዎድሮስ ምሳሌ በሣለው የራስ ምስልም ውስጥ እናገኘዋለን፡፡
‹‹ታዲያ እንግዲህ አንቺ ኢትዮጵያ እኛስ ልጆችሽ ምንድነን
አመንኩሽ ማለት እማንችል ፍቅራችን እሚያስነውረን
ዕዳችን የሚያስፎክረን
ቅንነት የሚያሳፍረን ቂማችን የሚያስደስተን
ኧረ ምንድነን? ምንድነን?››
አሜኬላ እሚያብብን
ፍግ እሚለመልምብን
ከአረም ጋር ያፈራን ጊንጦች ከእንክርዳድ ያልተለየን ዘር
ግርዱ ከምርቱ ተማጥቆ ከቶ ያልተበራየን መከር....››
በአዋሽ
ሥነ ግጥም የተሣለው የጸጋዬ ውስጣዊ የኪሳራ ስሜትና ትካዜ ተስፋ ላለመቁረጥ የተደረገ ውሳጣዊ ሙግት ነው፡፡
ይሁንና ይኸው ውሳጣዊ ትግል ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት የታሪካችን ጉዞ ምስልም
ነው፡፡
እሳት ወይ አበባ
እሳት ወይ
አበባ
ሌት ከዋክብቱ እንደ ፀደይ
አጥለቅልቆን በቀይ አደይ
ሰማዩ ሥጋጃ አጥልቆ
ተሽለምልሞ አንጸባርቆ
ፈክቶ አሸብርቆ ደምቆ
በአዝመራ በአጥቢያ ዐፀድ ሰፍኖ
የዓደይ አዝርዕት ተከሽኖ
በዕንቁጣጣሽ ሰብል ታጥኖ
ኢዮሃ አበባዬ ሆኖ፥
ጨረቃዋ ከቆባዋ፥ ከሽልምልሚት እምቡጧ
ጧ ብላ ከሰንኮፈንዋ፥ ተንዠርግጎ የእንኮይ ቡጧ፥
ድንግል ጽጌ-ረዳ ፈልቃ
ፍልቅልቂት ድምቡል ቦቃ …
ተንሠራፍታ የአበባ ጮርቃ፥
ታድያን ብሌኑ የጠጠረ
ባሕረ-ሃሳቡ የከረረ
የውበት ዓይኑ የታወረ
ልበ-ሕሊናው የሰለለ
አይ፥ አበባ አይደለም አለ፤
አይ፥ እሳት አይደለም አለ፤
ያልታደለ። …
ሰማይ ጨለማ ነው እንጂ፥ እሳት አደል ብሎ ካደ
እቶን ባይኑ እየነደደ።
ከዋክብቱ እንደ ችቦ
በነበልባል ወርቀ ዘቦ
ከፅንፍ ፅንፍ አውለብልቦ
ደመራው እየተመመ
እየፋመ እየጋመ
ደመና እንደንዳድ ሲነድ
መንጸባርቅ ሰደድ ሲወርድ፥
በራሪ ኮከብ ተኩሶ
በአድማሳት እሳት ለኩሶ…
ይኸ እንደኔና እንዳንቺው፥ የውበት ዓይኑ የሰለለ
ሰማይ ጨለማ ነው እንጂ፥ እሳት እኮ አይደለም አለ፥
ያልታደለ። …
… ይቅር ብቻ አንናገርም፥
እኔና አንቺ አንወያይም፤
ለውይይት አልታደልንም
እንዲያው ዝም፥ እንዲያው ዝም … ዝም።
አበባ አንሆን ወይ እሳት
ተጠምደን በምኞት ቅጣት
ሰመመን ባጫረው መዓት
ዕድሜ አችንን እንዳማጥናት፤ …
እሳት አንሆን ወይ አበባ
በሕቅ እንቅ ስንባባ
ባከነች ልጅነታችን፥ እየቃተትን ስናነባ
ሳንፈጠር በሞትንባት
ሳናብብ በረገፍንባት
ሳንጠና ባረጀንባት
አበባ ወይንም እሳት፥ መሆኑን ብቻ አጣንባት።
ሌት ከዋክብቱ እንደ ፀደይ
አጥለቅልቆን በቀይ አደይ
ሰማዩ ሥጋጃ አጥልቆ
ተሽለምልሞ አንጸባርቆ
ፈክቶ አሸብርቆ ደምቆ
በአዝመራ በአጥቢያ ዐፀድ ሰፍኖ
የዓደይ አዝርዕት ተከሽኖ
በዕንቁጣጣሽ ሰብል ታጥኖ
ኢዮሃ አበባዬ ሆኖ፥
ጨረቃዋ ከቆባዋ፥ ከሽልምልሚት እምቡጧ
ጧ ብላ ከሰንኮፈንዋ፥ ተንዠርግጎ የእንኮይ ቡጧ፥
ድንግል ጽጌ-ረዳ ፈልቃ
ፍልቅልቂት ድምቡል ቦቃ …
ተንሠራፍታ የአበባ ጮርቃ፥
ታድያን ብሌኑ የጠጠረ
ባሕረ-ሃሳቡ የከረረ
የውበት ዓይኑ የታወረ
ልበ-ሕሊናው የሰለለ
አይ፥ አበባ አይደለም አለ፤
አይ፥ እሳት አይደለም አለ፤
ያልታደለ። …
ሰማይ ጨለማ ነው እንጂ፥ እሳት አደል ብሎ ካደ
እቶን ባይኑ እየነደደ።
ከዋክብቱ እንደ ችቦ
በነበልባል ወርቀ ዘቦ
ከፅንፍ ፅንፍ አውለብልቦ
ደመራው እየተመመ
እየፋመ እየጋመ
ደመና እንደንዳድ ሲነድ
መንጸባርቅ ሰደድ ሲወርድ፥
በራሪ ኮከብ ተኩሶ
በአድማሳት እሳት ለኩሶ…
ይኸ እንደኔና እንዳንቺው፥ የውበት ዓይኑ የሰለለ
ሰማይ ጨለማ ነው እንጂ፥ እሳት እኮ አይደለም አለ፥
ያልታደለ። …
… ይቅር ብቻ አንናገርም፥
እኔና አንቺ አንወያይም፤
ለውይይት አልታደልንም
እንዲያው ዝም፥ እንዲያው ዝም … ዝም።
አበባ አንሆን ወይ እሳት
ተጠምደን በምኞት ቅጣት
ሰመመን ባጫረው መዓት
ዕድሜ አችንን እንዳማጥናት፤ …
እሳት አንሆን ወይ አበባ
በሕቅ እንቅ ስንባባ
ባከነች ልጅነታችን፥ እየቃተትን ስናነባ
ሳንፈጠር በሞትንባት
ሳናብብ በረገፍንባት
ሳንጠና ባረጀንባት
አበባ ወይንም እሳት፥ መሆኑን ብቻ አጣንባት።
No comments:
Post a Comment