Wednesday, May 9, 2012

በቴዲ አፍሮ “ጥቁር ሰው” ውስጥ የተዛባ የታሪክ ግድፈት የለም



www.facebook.com/tarikuasefa
ማንኛውም የኪነጥበብ ስራ ለህዝብ ሲቀርብ ከባለሙያም ሂስ፣ ከታዳሚ ደግሞ አስተያየት መሰጠቱ የሚጠበቅ ነው። ሆኖም ግን የግለሰቦች አስተያየት፣ ከአስተያየትነት አልፎ ሄዶ፣ ተጠባቢውን በመናቅ የጥበብ ስራውን አፍርሶ እንዲሰራ ለመጠቆም መሞከር፣ እጅግ ከጥበብ አለም ከራቀ ሰው ብቻ የሚደረግ ድፈረት ይመሰለኛል።

“የቴዲ አፍሮ “ጥቁር ሰው” እና ጥቂት የተዛቡ የታሪክ እውነቶች” በሚል አርዕስት ስር የቀረበውን መጣጥፍ አንብቤ እንደጨረስሁም የደረስሁበት ድምዳሜ፣ ከአስተያየቱ ገንቢነት ይልቅ፣ አስተያየቱን የሰነዘሩትን ግለሰብ፣ ግላዊ ጀብደኝነትን የሚያጎላ ሆኖ ነው ያገኘሁት።
ተችው ያቀረቡትን ነጥብ በማንሳት፣ በግሌ የሚታየኝን የማልስማማበትን ሃሳብ ከመሰንዘሬ በፊት ግን፣ በመግቢያየ ላይ የሰነዝርሁትን ሃሳብ፣ ከስነ-ግጥም ወጣ ባለ መልኩ፣ የግለሰቡን ትችት በሌላ የስነ-ጥበብ ክፍል እንዲመለከት እንባቢየን ልጋብዝ። “ጥቁር ሰው” የሚለው ሃሳብ ፡ በዜማ ስጋ እና አጥንት ጠንክሮ፣ በተዋቡ የግጥም ቃላቶች የደም ዝውውር ስላለውና ፤ ቃላትን ደግሞ አማርኛን ለመግባቢያነት የምንጠቀም ሁሉ፣ በቁሙ ከመተርጎም ጀምረን እንደፈለግን እከመተንተን ሃቅሙ ብቻ ስላለን፣ ያሻንን ልንል ቻልን እንጅ ፤ ይህ ግዙፍ የሆነ ሃሳብ፣ ሌላ የጥበብ ዘርፍ በሆነው በስነ-ስዕል ቢገለጽ ምን እንል ነበር። ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ፣ በአረንጓዴ ቀለም የሳሉትን የሰው ምስል “ጥቁር ሰው” ብለው ቢሰይሙት የምንሰጣቸው እርምት ምን ይሆን ነበር? ምናልባት ይህን ሃሳብ የሰነዘርሁት እንዲሁ ለልብ አድርቅ ክርክር ሳይሆን፣ እንዴውም በዚሁ በ “ጥቁር ሰው” አልበም ከተካተቱት ውስጥ፣ በግሌ የአንደኝነት ደረጃ በምሰጠው “ ስለ ፍቅር” በተሰኘው ዜማ ውስጥ …
አፈር ይዞ ውስጡ አረንጓዴ
ለምን ይሆን የራበው ሆዴ።
የሚል ስንኝ ተቋጥሮ እናገኛለን። ለመሆኑ ግን፣ የት አገር ነው አረንጓዴ አፈር ታይቶ የሚታወቅ?! መልሱ አንድ እና አንድ ነው፣ ኪናዊ ገለጻ በህግጋት የታጠረ አይደለም። የልቁንስ ተጠባቢው በህይወቱ በሚያካብተው የህይወት ነጸብራቅ ውስጥ እየተመራ፣ የራሱን ፍልስፍና ተንፍሶ እፎይ የሚልበት ነው።
እናም፣ ቴዲ አፍሮ በዚህ አልበሙ ውስጥ “በጥቁር ሰው” ዜማ ውስጥ የተካተቱት ታሪካዊ ጀግኖቻችን፣ በነጸብራቅነት የተጠቀሱበት እንጅ፣ የታሪክ ገድላቸው በዝርዝር የተዘከረበት አይደለም። ሊሆንም አይችልም። ሊሆንም አይጠበቅበትም። ምክንያቱም ስነ-ግጥም በትንታኔ መተረክ ስራው አይደለም። የከያኒውን ጥበባዊ ግዝፈት ወደ የቃላት ለቀማ ማውረድም ተገቢ አይደለም።
ለምሳሌ ትችቱን ያቀረቡት ግለሰብ “አባ ነፍሶ” የደጃዝማች ባልቻ የፈረስ ስም እንጅ የአባታቸው ስም አለመሆኑን መጥቀሳቸው፣ እንኳንስ የከያኒውን ይቅርና፣ የተደራሲውንም የግንዛቤ ደረጃ ያልተረዱ አስመስሎባቸዋል። ይህን አስተያየታቸውን ሳነብ፣ ቴዲ አፍሮ በ “ያስተሰርያል“ አልበሙ ላይ “ሸመንደፈር” ዘፈኑን የሰማ አንድ ጓደኛየ የተሰማውን ቁጣ አስታወሰኝ። ይህ ጓደኛየ በዚህ ዘፈን ላይ ያለው ትችት፣ ቴዲ አፍሮ “ሙስሊም እና ክርስቲያን ቢጋባ” ብሎ የመከረ ያህል አድርጎ እንጅ የተረዳው፣ ስለኢትዮጵያዊነት በሃይማኖት የመቻቻል፣ ታላቅ እሴት ገለጻ አድርጎ አልነበረም የተረዳው። ልክ እንደዚያው ሁሉ፣ “ባልቻ አባቱ ነፍሶ” የሚለውን ሃረግ፣ ሙሉ በሙሉ በቁሙ ከመተርጎም ይልቅ፣ ቴወድሮስ ለማለት የፈለገው “ምን ይሆን?” ብሎ ጥበብን መመርመር ተገቢ ነው። ጥበብ ሲመረመር ግን፣ በቁጥብ ቃላት የተገለጸን ሃሳብ ዝርዝር ወደ ሆነ ተረት ተረት መቀየር ማለት አይደለም። ስለዚህ፣ የዚህን ሃሳብ ምንነት መተቸቱን የምቃወመውን ያህል፣ የተቃና ትርጉም ለመስጠት ብሞክር ግን የአስተያየቴን አቅጣጫ ያስተዋል ብየ አምናለሁ። እኔ ከምለው የተሻለ ግን ፡ አቶ ዳዊት በራሱ የብዕር ሰይፍ የራሱን ሃሳብ ቀንጥሶ ሲጥል፣ “ፊአውራሪ ገበየሁን አርበኛው ሲያወድሳቸው፣ በረፈረሳቸው ስም “እረ ጎራው” ይላቸዋል” ይላል። ታዲያ የዛን ዘመን ገጣሚ ጀግናን በፈረሱ ስም ከጠራው የዚህ ዘመኑ ቴዲ አፍሮ ደግሞ የጀግናውን ባልቻ አባት በጥበባዊ ገለጻ የፈረሱን ስም ቢሰጠው ምኑ ላይ ነው የታሪክ ግድፈቱ?!
ከዚህም በተጨማሪ፣ ትችት ሰንዛሪው ያቀረቡትን ሁለተኛ ነጥብ ቃል በቃል ለመተቸት እወዳለሁ። “ መድፉን ጣለው ተኩሶ” የሚለው የሙገሳ ስንኝ ከደጃዝማች ባልቻ ይልቅ፣ ለሊቀ መኳስ አባተ የሚገባ አድርገው ትችት ሰንዝረዋል። ለመሆኑ በግጥም ስንኝ ውስጥ የሚሰነዘሩ ሃሳቦች፣ በቁጥብ ቃላት በርካታ ሃሳቦች መሆኑን ተረድተውት ይሆን ግለሰቡ?! ደጃዛማች ባልቻ መድፈኛ ለመሆናቸው እና የመድፈኝነት ጀግንነታቸውንም እንኳንስ ሊቀመኳስ አባተ ቀርቶ፣ ፊታውራሪ ገበየሁ እንደሚቀድሟቸው ተከታዩ የወቅቱ ግጥም ይገልጻቸዋል፦
ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ
መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ።
ታዲያ የቴዲ ግጥም የደጃዝማች ባልቻን መድፈኝነት ከአድዋ ጋር ከማቆራኘት ያለፈ ምን የታሪክ ዝንፈት አስገባ?! የልቁንስ የከያኒው ቁጥብ ገለጻ፣ እንደዚህ የተለያዩ ሃሳቦችን እያነሱ ለመወያየት ይረዳ እንደሆነ እንጅ?!
እንዴውም ከታሪክ አንጻር እንነጋገር ከተባለማ ፀሃፊው፦
የአድዋ ስላሴን፣ ጠላት አረከሰው፤
ገበየሁ በሞቴ፣ ግባና ቀድሰው።
የሚለውን ግጥም አስታክከው፣ ጸሃፊው አዛብተው እንዳቀረቡት፣ “ሰራዊቱ ጦርነቱ የሚጀመርበትን ቀን መናፈቅ ጀምሮ ፊታውራሪ ገበየሁን በግጥም ሸነጥ” ለማድረግ ሳይሆን ፤ ግጥሙ የተገጠመው ከጦርነቱ በኋላ ሲሆን ፤ የግጥሙ ታሪካዊ ምንጭም እንደሚከተለው ነው።
ጣሊያኖች እንዳ ስላሴ ብቻ ሳይሆን፣ በሁሉም የጦር አቅጣጫቸው ከትመው ጦርነት ማድረግ አይፈልጉ የነበረበት ምክንያት፣ በበርካታ ሽህ ህዝብ የሚቆጠረው ኢትዮጵያዊ ሰራዊት፣ በእግሩ እና በፈረስ ብቻ ሩቅ ተጉዞ የመጣ በመሆኑና፣ ጦርነቱ ሳይደረግ ትንሽ ቀናት ከቆየ፣ ይዞት የመጣውን ስንቅ በልቶ ይጨርሰውና፣ ጣሊያኖች ብዙም መቋቋም ሳይገጥማቸው በቀላሉ ለማሸነፍ የወጠኑትን የጦርነት ስልት ነበር። ይህንም ስልት ለማክሸፍ ነው ፊታውራሪ ገበየሁ ጦርነቱን የቀደሰው እንጅ፣ ሰዎች በግጥም ገፋፍተውት አይደለም። ይህም በንጉስ ምኒሊክ ዘንድ ከበሬታ ያስቸረውን ያህል፣ አደገኛ የተናጠል ድርጊት ተደርጎ ተወስዶበት በወቅቱ በንጉስ ምኒሊክ እንዳስተቸው በታሪክ ተጽፏል። እናም ግጥሙ የተገጠመው ከእንዳ ስላሴው ጦርነት በኋላ እንጅ በፊት አይደለም። ይህንም ያነሳሁት፣ እንድትልቅ ልዩነት ለማሳየት ሳይሆን ፤ እንኳንስ ለዘፈን በሚደረስ ምጥን ስነ-ግጥም ውስጥ ቀርቶ፣ ያሻን ያህል ቃላት ተጠቅሞ በሚቀርብ መጣጥፍም፣ ሃሳብ ምን ያህል ሊመዛበር እንደሚችል ለመግለጽ ብቻ ነው።
የፊታውራሪ ሃብተጊዮርጊስም ጉዳይ፣ እንዲሁ የቃላት እሰጥ አገባ ካልሆነ በቀር፣ ትችቱን የሰነዘሩት ግለሰብ የመነሻም ሆነ የመድረሻ ሃሳባቸው መሆን የነበረበት፣ ሌላው እንኳን ቢቀር “የሃብተጊዮርርጊስ የማዕረግ ስማቸው ማን ነበር?” የሚለው ነው። መልሱም “ፊታውራሪ” ነው። ከዚህ በኋላ ያለው ትንታኔ ለታሪክ አስተምሮት የሚጥቀም እንጅ፣ ኪነትን ለመሞገት ሃቅም ያለው የመከራከሪያ ሃሳብ አይደለም።
እንዴውም ትችት አቅራቢውን ሊገርማቸው በሚችል መልኩ፣ ቴዲ አፍሮን በዚህ አልበሙ “ጥቁር ሰው” እያለ ያሞካሻቸው እምዬ ምኒሊክ፣ በታሪክ አጋጣሚ በአንድ ወቅት እራሳቸውንና ኢትዮጵያውያንን “ኒግሮ ወይም ጥቁር አይደለንም” እንዳሉ ታሪክ ዘግቦታል። ይህ ግን በወቅቱ የነበረውን አመለካከት ብቻ ሳይሆን፣ እስከአሁንም ድረስ እራሱን ከሌሎች አፍሪካውያን ልዩ አድርጎ የሚቆጥር ኢትዮጵያዊን የሚገልጽ ቢሆንም ፤ ዘመን ተሻጋሪ የጥበብ ስራዎችን እያቀረበ ያለው ቴዲ አፍሮ የሰጣቸው ስያሜ ግን፣ እምዬ ምኒሊክ ከአደዋ ድል ማግስት ድላቸው የሁሉም ጥቁር ህዝብ መሆኑ እና እኛም ጥቁርነታችን ምድር ላይ የሚስተዋል ሃቅ መሆኑ ነው። አጼ ምኒሊክን “ጥቁር አይደለሁም” ብለው ነበር ብሎ የሚተች ትውልድ ቢኖር፣ አቶ ይድነቃቸው ተሰማ “ለአውሮፓ አገር በፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋችነት፣ በሚሊዮን ዶላር መሸጥ ባርነት ነው” ማለታቸውንም በዘመን ሚዛን ሊለካ ይገባል።
በመጨረሻም፣ ታላላቅ የኪነጥበብ ስራዎች አይነተኛ መለያቸው ህበረተሰብን ለውይይት የማነሳሳት ሃቅማቸው ቢሆንም ፤ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸው ሃሳቦች ግን ከውይይት አልፈው ከያኒውን የመጠምዘዝ ሃይል ይኖራቸዋል ማለት አይደለም። ውስጣዊ ፍልስፍናውን በሰዎች አስተያየት የሚቃኝ ከያኒ ቢኖር፣ ፍጹም የኪነት ሰው ሳይሆን ፤ አሁን አሁን እንደምናያቸው ያሉ ለጥቅም የተሰማሩ፣ ልማታዊ አርቲስቶች እና የገንዘብ ሰራዊቶችን ይመሰላል።

No comments:

Post a Comment