www.facebook.com/tarikuasefaየድንቆች ምድር ኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ቀልብ መሳብ የሚችሉ በርካታ ሀብቶችን ከታደሉ ጥቂት የዓለማችን ሀገሮች አንዱዋ ነች፡፡
ኢትዮጵያ የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤትም ነች፡፡ የቀደምት ስልጣኔዋ አሻራ የሆኑ ብዙ ባህላዊ ታሪካዊና የቱሪስት መስህብ
ሀብቶች አሏት፡፡
ከዚህ
ሌላ ኢትዮጵያ ከ80 በላይ የሆኑ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በሰላምና በመቻቻል የሚኖሩባት ሃገር ናት፡፡
በዚህም የብሄረሰቦችና ቋንቋዎች ሙዚየም ለመባል በቅታለች፡፡ ሃገራችንን በአለም ላይ ታዋቂ ያደረጋት ሌላው ገጽታ
ደግሞ የተለያዩ እምነቶች ተከታይ የሆኑ ህዝቦች በመተሳሰብ በጋራ የሚኖሩባት ሃገር መሆኗ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከተቀረው
ዓለም በተለየ የራሷ የሆነ የዘመን አቆጣጠር አላት፡፡
ከዘመን
አቆጣጠሩ ጋር ተያይዘው በህዝቦችዋ የሚከበሩት የሃይማኖት በዓላት /Festivals/ በርካታ ቱሪስቶች ወደ
ሃገራችን እንዲጎርፉ የማድረግ አቅም አላቸው ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ በእንግዳ ተቀባይነቷ፣ በሰው ዘር
መገኛነቷ፣ በነጻነት ተምሳሌትነቷ ትታወቃለች፡፡
ለመሆኑ
የኢትዮጵያን የቱሪሰት መስህብ ሃብቶች በአግባቡ ያውቃሉ? ጥቂቶቹን እናስተዋውቅዎ፡፡ ሃገራችን ካሏት ድንቅ
የቱሪሰት መስህብ ሃብቶች ውስጥ ዘጠኙ በተባበሩት መንግስታት የሳይንስ፣ የባሀልና ትምህርት ድርጅት /UNESCO/
በዓለም ቅርስነት ተመዝግበዋል፡፡
በዩኔስኮ በአለም ቅርስነት የተመዘገቡ ዘጠኙ የኢትዮጵያ ቅርሶች
1.የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን
በአማራ
ክልል በሰሜን ወሎ ዞን ከቆቦ ከተማ 78 ኪ.ሜ ገባ ብላ የምትገኘው የላሊበላ ከተማ በጥንት ዘመን ሮሃ ተብላ
ትጠራ ነበር፡፡ ላሊበላ የሚለውን ስም ያገኘችው አስራ አንዱን ውቅር አብያተ ክርስቲያን ከአንድ ወጥ ድንጋይ
አስፈልፍለዋል ተብለው ከሚነገርላቸው ከዛጉዌ ነገስታት አንዱ ከሆኑት ከአጼ ላሊበላ ነው፡፡
በ12ኛው
መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ተፈልፍለው እንደታነጹ የሚነገርላቸው እነኝህ 11 አብያተ ክርስቲያን
በአስደናቂነታቸው ወደር ያልተገኘላቸው ናቸው፡፡ በርካታ ተጓዞችና የጉዞ ጸሀፍት የላሊበላን አብያተ ክርስቲያን
የኢትዮጵያ ዋና የቱሪስት መስህብ ሃብት “prime tourist attraction of Ethiopia” ብለው
ይገልጹአቸዋል፡፡ ይህ ድንቅ የአባቶች ጥበብ እ.ኤ.አ ሴፕቴምበር 8/1978 በተባበሩት መንግስታት የትምህርት
የሳይንስና የባህል ድርጅት ማህደር ውስጥ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ የመጀመሪያው የአገራችን ቅርስ ነው፡፡
2. የጎንደር አብያተ መንግስት ግብረ ህንጻ
የኢትዮጵያ
ጥንታዊ ከተሞች ታሪክ ሲወሳ የጎንደር ስም ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡ የጎንደር ነገስታት ግብረ ህንጻዎች በአማራ
ክልል ከአዲስ አበባ ሰሜን ምዕራብ 738 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ከተማ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በ17ኛው ክፍለ ዘመን
የመጀመሪያው አጋማሽ በአጼ ፋሲለደስ ዘመን መንግስት እንደተቆረቆረች የሚነገርላት ጎንደር ከሌሎች ቀደምት ከተሞች
ለየት የሚያደርጋት ለረጅም ጊዜ በመናገሻ ከተማነት ማገልገሏ ነው፡፡ በታሪክና በባሀል ነጸብራቅነቷም ትታወቃለች፡፡
የጎንደር ከተማ ዋነኛ የቱሪስት መስህብ ሃብቶች የመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ነገስታት ያሰሯቸው አብያተ መንግስትና
አብያተ ክርስቲያን ናቸው፡፡ አብያተ መንግስቱ በከተማ መሃል በሚገኘው ከፍተኛ ስፍራ ላይ ከአጼ ፋሲል ግቢ ቀደም
ሲል 12 በሮች እንደነበሩት ይነገራል፡፡ አሁን ያለው የመግቢያ በር ከጥንቶቹ በሮች አንዱ ሳይሆን በጣሊያን ጊዜ
የተሰራ ነው፡፡ አብያተ መንግስቱ የተሰሩት ከድንጋይ ፣ ከእንጨትና ከኖራ ሲሆን የጥንት
ኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ረቂቅነትን ያንጸባርቃሉ፡፡ ይህን አገራችን የራሷ ግብረ ህንጻ አሰራር እንደነበራት በዓለም
የመሰከረውን ግብረ ህንጻ የተባበሩት መንግስታት የትምህርት ፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት /UNESCO/ እ.ኤ.አ
ኦክቶበር 1979 በዓለም ቅርስነት መዘግቦታል፡፡
3. የአክሱም ሐውልቶች የአካባቢው አርኪኦሎጂያዊ ሥፍራ
ከአዲስ አበባ ከ1000 ኪ.ሜ ርቃ በትግራይ ብሄራዊ ክልል የምትገኘው የአክሱም ከተማ < የኢትዮጵያ የጥንት ዘመን ከተማ> (Ethiopia’s most ancient city) ትባላለች፡፡
በ3ኛው
ክፍለ ዘመን በወታደራዊ ሃይልና በንግድ እንቅስቃሴያቸው የታወቁት 4 ትልልቅ ግብአቶች ባቢሎን ፣ ሮማ ፣ ግብጽና
አክሱም እንደነበሩ የታሪክ መጽሐፍት ያስረዳሉ፡፡ አክሱም ጥንታዊ ቀርሶች ፣ አስደናቂ ሃውልቶች ፣ ቤተክርስቲያኖች፣
የነገስታት መቃብሮችና የቤተ መንግስት ፍርስራሾች የሚገኙባት በቱሪስት መስህብ ዝነኛ የሆነች ከተማ ነች፡፡ ጽላተ
ሙሴ አርፎባታል ተብሎ የምትገመተው የአክሱም ጽዮን ማርያም ቤተክርስቲያን የምትገኘውም በዚህች ጥንታዊና ታሪካዊ
ከተማ ውስጥ ነው፡፡
የአክሱምን ሃውልቶች የተመለከተ ሁሉ የተሰሩበት ዘመን ወደ ኋላ በመቃኘት እነዚያ ግዙፍ ድንጋዮች በዚያ ዘመን እንዴት ሊቆሙ እንደቻሉ መደነቁ የማይቀር ነው፡፡
በአክሱምና
በአካባቢዋ ካንድ ወጥ ድንጋይ ተፈልፍለው የተሰሩ ከሃምሳ በላይ ሐውልቶችና የሰው ልጅ ጥንታዊ የእጅ ጥበብ
ውጤቶችን በተባበሩተ መንግስታት የትምህርት ፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት እ.ኤ.አ ሴፕቴምበር 1980 በዓለም
ቅርስነት መዘግቧቸዋል፡፡ ከአክሱም ሐውልቶች መካከል አንዱ የሆነውና 24.6 ሜትር ርዝመት ያለው እ.አ.አ በ1937
ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረች ጊዜ በፋሽስት ወታደሮቿ ተዘርፎ ወደ ሮም ተወስዶ ነበር፡፡ ይህ ሐውልት ለ68 ዓመታት
በሮም አደባበይ ተተክሎ ከቆየ በኃላ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ባደረጉት ያላሰለሰ ጥረት በሚያዝያ ወር 1997
ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሷል፡፡ ሐውልቱ በሶስት ቦታዎች ተከፍሎ በግዙፍ ዕቃ ጫኝ አውሮፕላን በሶስት ጊዜ ምልልስ
የመጣ ሲሆን የመልሶ ተከላ ስራው ሲነከናወን ቆይቶ ነሃሴ 29/2000 ተመርቋል፡፡
4.ሐረር ጀጎል ግንብ
ጥንታዊቷ
የሐረር ከተማ በምስራቅ ኢትዮጵያ ከአዲስ አበባ 525 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ ከ7ኛው አስከ 9ኛው መቶ
ክፍለ ዘመን እንደተቆረቆረች የሚነገርላት የሐረር ከተማ አምስት በሮች ባሉትና ጀጎል ተብሎ በሚጠራው ዝነኛ አጥር
/ግንብ/ የተከበበች ናት፡፡ ግንቡ ከ13ኛው እስከ 16ኛው መቶ ክ/ዘመን እንደተሰራ የሚነገር ሲሆን የተሰራበት ዋና
አላማም ወራሪዎችን ለመከላከል እንደሆነ ይነገራል፡፡
ይህ ታሪካዊ ግንብ ለጎብኚዎች እንደ መስህብ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ሐረር
ስትቆረቆር ተሰራ ተብሎ ከሚታመነው ጥንታዊ የሼክ አባድር መስጊድ ሌላ ስድስትና ሰባት መቶ አመት እድሜ ያላቸው
ጥንታዊ ቤቶች ፣ የአቡ ሰኢድ አሊ መቃብር ቦታ ፣ በጥንታዊ ሰዎች የተሳሉ የዋሻ ውስጥ ስዕሎች አሉ፡፡
ከዚህ
ሌላ ሐረር አንጋፋ የንግድ መናኸሪያ እና የእስልምና ትምህርት ማዕከል እንደነበረች ከታሪክ እንረዳለን፡፡ በከተማዋ
ውስጥ ከ90 ያላነሱ መስጊዶች ያሉ ሲሆን 4ኛው የእስልምና ሃይማኖት ቅዱስ ከተማ ተብላ ትጠራለች፡፡ የከተማዋ
መንገዶች ጠባብነት ፣ የቤት አሰራራቸው ቅርጽ ልዩ መሆን ፣ ጅብን የመመገብ ባህል ፣ ሴቶቻቸው የሚለብሷቸው ደማቅ
ቀሚሶች፣ ልዩ ልዩ የዕደ ጥበብ ስራዎቻቸው ፣ ሐረርን ከሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች የተለየች የቱሪስት መዳረሻ
ያደርጓታል፡፡
ሐረር ከምስራቅ አፍሪካ ጥንታዊ ከተሞች አንዷ መሆኗን በማመን የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት እ.ኤ.አ በ2006 በዓለም ቅርስነት መዝግቧታል ፡፡
5. የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ
ኢትዮጵያ
ውስጥ ከሚገኙ አንጋፋ ብሄራዊ ፓርኮች አንዱ የሆነው የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የሚገኘው በአማራ ክልል ሰሜን
ጎደር ዞን ከደባርቅ ከተማ 32 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ነው፡፡ ፓርኩ ከባህር ወለል በላይ ከ1900-3926 ሜትር ከፍታ
ላይ ይገኛል፡፡ ከፓርኩ ተራሮች ጋር ተያይዞ የሚገኘው በከፍታው ከሀገራችን አንደኛ ከአፍሪካ ደግሞ 4ኛ የሆነው ራስ
ዳሽን ተራራ ከፓርኩ የማረፊያ ሰፈር በሁለት ቀን የእግር ጉዞ ላይ ይገኛል፡፡ የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ
ውስብስብ የተፈጥሮ ትንግርት የሚታይበት ስፍራ ነው፡፡
ኢትዮጵያ
ውስጥ ብቻ ከሚገኙት ሰላሳ አንድ ጡት አጥቢ የዱር እንስሳት ሰባቱ ፣ ከአስራ ስድስት አእዋፋት ደግሞ አስራ ሶስቱ
የሚገኙት በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ውስጥ ነው፡፡ ዋልያ፣ የሰሜን ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮ የፓርኩ ልዩ
መታወቂያዎች ናቸው፡፡ ሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት
እ.ኤ.አ በ1978 በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል፡፡
6. የታችኛው ኦሞ ሸለቆ የቅርስ ሥፍራ
የታችኛው
ኦሞ ሸለቆ የቅርስ ሥፍራ በደቡብ ብሄር ብህረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት በደቡብ ኦሞ ዞን መስተዳድር ውስጥ
ይገኛል፡፡ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ቱርካና ሐይቅ አካባቢ የሚገኘው የታችኛው ኦሞ ሸለቆ በሰው ልጅ አመጣጥና ቅድመ
ታሪክ ጥናት ከፍተኛ ሥፍራ የሚሰጠው ቦታ ነው፡፡
ከ2.4
ሚሊዮን አመት በላይ እድሜ ያላቸው ጥንታዊ ቁሳቁሶችና የሰው ዘር ቅሪተ አካሎች የተገኙበት ይህ አካባቢ የተለያዩ
ጥንታዊ ባህላቸውንና አኗኗራቸውን የሚከተሉ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የሚኖሩባት በመሆኑ አንትሮሎጂስቶች በብዛት
የሚጎርፉበት አካባቢ ነው፡፡ እጅግ በጣም በርካታ ባህላዊ ትውፊቶች በውስን አካባቢ የሚገኙበት መሆኑ የታችኛውን
የኦሞ ሸለቆ በዓለም ልዩ ሥፍራ ያደርገዋል፡፡ ይኸው ሥፍራ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት ፣ የሳይንስና የባሀል
ድርጅት እ.ኤ.አበሴፕቴምበር 1980 በአለም ቅርስነት ተመዘግቧል፡፡
7.የጥያ ትክል ድንጋዮች
የጥያ ትክል ድንጋዮች በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት በጉራጌ ዞን ሶዶ ውስጥ ከመልካ ቁንጥሬ 40 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛሉ፡፡
ትክል ድንጋዮችን ለቀብር ቦታ ምልክትነት በመጠቀም ከቀብር ሰርዓት መጀመር ጋር አብሮ ያደገ ባሀል ነው፡፡
የትክል ድንጋዮች አይነት የተለያየ ሲሆን ከአንድ ሜትር ቁመት በታች ካላቸው አንስቶ እንደ አክሱም ሐውልቶች በትክክል ተቀርጸው የቆሙ ረጃጅም ግዙፍ ትክል ድንጋዮች ድረስ አሉ፡፡
ሶዶና
አካባቢው ከአምስት የማያንሱ የትክል ድንጋይ አይነቶች የሚገኙ ሲሆን ፣ ከነኝህ መካከል ባለ ሰው ቅርጽ
/anthropomorphic steale/፣ ምስሎች የተቀረጹባቸው ድንጋዮችና/Figurative steale/ የወንድ
ብልት ቅርጽ ያላቸው /Sword steale/ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የጥያ መካነ ቅርስ የአለም ህዝቦች የጋራ እሴት
ተደርጎ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት ፣ የሳይንስና የባሀል ድርጅት እ.ኤ.አ ሴፕቴምበር 5/1980 በዓለም
ቅርስነት የተመዘገበው ከዚህ ታሪካዊ ፋይዳው የተነሳ ነው፡፡
8. የታችኛው አዋሽ ፓሊዮአንትሮፖሎጂና ቅድመ ታሪክ ሥፍራ
በአፋር ብህራዊ ክልላዊ መንግስት የታችኛው አዋሽ ተፋሰስ ወስጥ የሚገኘው ሃዳር በዓለም ታዋቂና ዝነኛ የሆነች የሰው ዘር ግንድ ቅሪተ አካል ሉሲ /ድንቅነሽ/ የተገኘችበት ሥፍራ ነው፡፡
አካባቢው
በአፍሪካ አህጉር በጣም ጠቃሚ የሆኑ ፖሊዮ አንትሮፖሎጂና ቅሪተ አካሎች የሚገኙበት ስለሆነ የሰው ዘር ምንጭና
ባህል አጥኚ ምሁራን ቀለባቸውን ኢትዮጵያ ላይ እንዲያሳርፉ አስገድዷቸዋል ፡፡ የ3.5 ሚሊዮን ዓመት እድሜ ያላት
ሉሲ/ድንቅነሽ እ.ኤ.አ በ1974 መገኘት የሰው ልጅ ቆሞ መሄድ እንደጀመረ ፍንጭ የሚሰጥ እንደሆነ ሳይንቲስቶች
ይናገራሉ ፡፡ በመሆኑም ይህንን ሥፍራ የተባበሩተ መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሀል ድርጅት እ.ኤ.አ
5/1980 በዓለም ቅርስነት መዝግቦታል፡፡
9.የኮንሶ ባህላዊ መንደሮች
የኮንሶ
ባሀላዊ መልክዓምድር በደቡብ ኢትዮጵያ ኮንሶ ከፍታዎች ላይ የሚገኝ 55 ሰኩዌር ኪ.ሜ የሚሸፍን በድንጋይ የታጠሩ
እርከኖችና የተመሸጉ መንደሮች ያሉበት ደረቅ ስፍራ ነው፡፡ ቅርሱ የ21 ትውልዶች /400 ዓመታት በላይ/ የኋላ
ታሪክ ያለው ሲሆን ደረቅና አስቸጋሪ ከሆነ አካባቢ ጋር ተስማምቶ የመኖር ሕያው ባህላዊ ልማድ አስደናቂ ምሳሌ
ነው፡፡ ቦታው የማህበረሰቡን የጋራ እሴቶች፣ ማህበራዊ ቁርኝትና የምህንድስና ዕውቀትን የሚያሳይ ነው፡፡ ሥፍራው
በተባበሩተ መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሀል ድርጅት እ.ኤ.አ ጁን 27/ 2011 በዓለም ቅርስነት
ተመዝግቧል፡፡
No comments:
Post a Comment